መንግሥት ሰላም ለማስፈን እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ጠየቁ

ኃይለማርያም ደሳለኝ

ሰኔ 17/2014 (ዋልታ) ሰላምን ለማስፈን መንግሥት እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር እርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጠየቁ፡፡

በዛሬው ዕለት በጎንደር ከተማ በተጀመረው 4ኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባደረጉት ንግግር ሰሞኑን በምዕራብ ወለጋ በጽንፈኞችና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ባለሙ እኩይ ኃይሎች በንጹሃን ላይ የደረሰውን ጥቃት አውግዘዋል፡፡

በሀገራችን ሰላም እንዲያሰፍንና ዜጎች በሰላም እንዲኖሩ መንግሥት አስፈላጊውን ሕግ የማስከበር ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

4ኛው የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራችንን በተሳካ መንገድ በመከወን ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበስ ዕቅዳችንን ልናሳካ ይገባል ያሉት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማድረግ ህልማችንን ለማሳካት ሁሉም ሰው በየተቋማቱና በመኖሪያ ቤቱ ችግኞችን እንዲተክል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ዛሬ በክልሉ የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብርም በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

ኅብረተሰቡ የደንን ጥቅም በውል ተገንዝቦ ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ ደን ሊፈጥር ይገባል ማለታቸውን የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ-ክርስቲያን ደን በመትከል ያላትን ተሞክሮ መቅሰም ይገባናል ሲሉም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

እኛ ሰዎች በደን ላይ ባደረግነው ጭፍጨፉ የተፈጥሮ ሚዛን ችግር ገጥሞናል፤ ይህን ችግር ለመፍታት በግለሰብና በተቋማት ደረጃ ችግኝ መትከልና መንከባከብ ይገባል ሲሉም መናገራቸውን የጎንደር ከተማ ኮሙዩኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።