ከ40ሺሕ በላይ ዜጎችን ከሳውዲ አረቢያ መመለስ ተችሏል

ሰኔ 18/2014 (ዋልታ) ከሳውዲ አረቢያ በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ እስካሁን ድረስ ከ40ሺሕ በላይ ዜጎችን መመለስ መቻሉን አስታወቀ።
16 የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን ያካተተው ብሔራዊ ኮሚቴ ባለፉት ወራት በችግር ላይ ያሉ ዜጎችን ለማስመለስ በተደረገው ጥረት ዙሪያ ውይይት አድርጓል።
ስብሰባውን የመሩት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሲራጅ ረሽድ እስካሁን 111 ጊዜ በተደረጉ በረራዎች 40 ሺሕ 794 ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለስ ተችሏል ነው ያሉት።
102 ሺሕ ዜጎችን ለማስመለስ ከተያዘው ዕቅድ አንጻር እስከ አውሮፓውያኑ ሰኔ 22 ድረስ ማሳካት የተቻለው 40 በመቶ እንደሆነ ገልጸዋል።
በቀጣይም ዜጎችን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የሚታዩ ክፍተቶችን በማረም በተቻለ ቅንጅታዊ አሰራር የታቀደውን ግብ ለማሳካት በትብብር መንቀሳቀስ እንደሚገባ ተነስቷል።
በተጨማሪም በተለያዩ የአፍሪካ አገራት በችግር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንንም ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ራሱን በቻለ የድርጊት መርኃ ግብር ተዘጋጅቶ እየተሰራ መሆኑ በውይይቱ ተጠቅሷል።