የህግ ማስከበሩን ሥራ ይበልጥ በማጠናከር የተረጋጋች ሀገር ለመገንባት የተጀመረው ሥራ ይቀጥላል ተባለ

ሰኔ 19/2014 (ዋልታ) የህግ ማስከበሩን ሥራ ይበልጥ በማጠናከር የተረጋጋች ሀገር ለመገንባት የተጀመረው ሥራ የሚቀጥል መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተናገሩ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን በአዲስ አበባ ያካሄደ ሲሆን በስብሰባው በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና የሰላም ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርጓል፡፡

የፓርቲው ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት በስብሰባቸው ከሰሞኑን በምእራብ ወለጋና በጋምቤላ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት አውግዘዋል።

በቀጣይ የጥቃቱን ተጎጂዎች መደገፍና ህግ የማስከበር ሥራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በውይይታቸው አጽኖት ሰጥተዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ጥቅማቸው የቀረባቸው የውስጥ ተላላኪዎች ከውጭ ጠላቶች ጋር ኅብረት በመፍጠር በዜጎች ሰላምና ደኅንነት ላይ አደጋ ለማድረስ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ነው የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የገለጹት፡፡

በተመሳሳይ ሌላኛዋ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ቡዜና አልቃድር የተዳከመችና የተበታተነች ኢትዮጵያን ማየት የሚሹ የውጭ ጠላቶችና የውስጥ ተላላኪዎች ሰላማዊ ዜጎችን በማጥቃት ለውጡ ይዞት የመጣው ትልም አውን እንዳይሆን መስራታቸውን ያብራራሉ፡፡

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት ኦሞድ ኡጁሉ በለውጡ ጥቅማቸው የተነካባቸው አካላት በተቀናጀና በተናበበ መልኩ ሰለማዊ ዜጎች ላይ የተነጣጠረ ጥቃት በመፈጸም ለውጡን ለመቀልበስ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዋናነት በንጹሃን ዜጎች ደም ወደ ስልጣን ለመምጣት የሚያደርጉት ጥረት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የማእከላዊ ኮሚቴ አባላቱ አብዱረህማን እድሪስና ኦድሪን በድሪ፤ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ የጽንፈኝነትና የአክራሪነት አዝማሚያዎች በዜጎች ሰላምና ደህንነት ላይ እንቅፋት መፍጠራቸውን አንስተዋል፡፡

የውጭ ጠላቶች እና የውስጥ ተላላኪዎች የጽንፈኝነትና የአክራሪነት አካሄዶች ይበልጥ እንዲስፋፉ ተቀናጅተው በመስራት በሰላማዊ ዜጎች ህይወት ላይ አደጋ እንዲፈጠር ማድረጋቸውንም ነው ያነሱት፡፡

በዚህም ዜጎች የሰላምና ደህንነት ጥያቄ በስፋት ሲያነሱ መቆየታቸውን ጠቅሰው መንግስት በተቀናጀ መልኩ የህግ ማስከበር ስራ በማከናወን ለዜጎች ጥያቄ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ማንም ቢሆን ከህግ በታች ነው የሚሉት አቶ ኦሞድ፤ መንግስት የህግ የበላይነትን በማስከበር የተረጋጋች አገር ለመገንባት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ህግ የማስከበሩ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የፓርቲው ማእከላዊ ኮሚቴም የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቁ ስራ በተቀናጀ መልኩ እንዲከናወን አቅጣጫ ማስቀመጡን ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ ኃላፊነታቸውን የማይወጡ አመራሮች ተጠያቂ ይሆናሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።