ም/ጠ/ሚኒስትሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሲተገበር የቆየ ጫና ማቅለያ ልምድ ነው አሉ

ሰኔ 20/2014 (ዋልታ) የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በማኅበረሰቡ ዘንድ ሲተገበር የቆየ ጫና ማቅለያ ልምድ ነው ሲሉ የኢፌድሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ እና የወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ባስጀመሩበት ወቅት ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት ወጣቶች በተሰማሩበት መስክ ለኅብረተሰቡ የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት ችለዋል ነው ያሉት።

ዘንድሮም ባለፉት ጊዜያት የተከናወኑ በጎ ልምዶችን መነሻ በማድረግ ሕዝቡ ሀገሪቱ ቅድሚያ የምትሰጠውን አጀንዳ ቅድሚያ በመስጠት መሰማራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

ሀገሪቱ በአንድ በኩል እያከናወነች ባለችው የልማት ሥራዎች ቀና ስትል በሌላ በኩል በዜጎች ላይ የሚስተዋል ጭፍጨፋና ግድያ አንገት እንድትደፋ አድርጓታል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ የጀመረውን የህግ ማስከበር እርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የዜጎች ደኅንነት ማስጠበቅ ሥራ ላይም ሁሉም ሊረባረብ ይገባል፤ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችም ወደ ማኅበረሰቡ ሲገቡ ሀገራዊ ጥረቱን ያጠናክረዋል ብለዋል።

ወጣቶች የሀገሪቱ የአብሮነት፣ የሰላም፣ የሥራና የተግባር አምባሳደር መሆናቸውን በመግለፅም የባንዲራ ርክክብ በማድረግ ለወጣቶች ሽኝት አድርገዋል።

በትዕግስት ዘላለም