ለአማራ ክልል መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ከ6 ሚሊየን ዶላር በላይ የድጋፍ ስምምነት ተፈረመ

ሰኔ 20/2014 (ዋልታ) የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ በክልሉ ለመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ድጋፍ የሚሆን 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር የእርዳታ ስምምነት ፕሮጀክት ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ጋር ተፈራርሟል።

ስምምነቱን የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን መሐሪ (ዶ/ር) እና በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ዋና ተጠሪ ሚስተር ቱርሃን ሳለህ ተፈራርመዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት በክልል ደረጃ ወደ አማራ ክልል ገብቶ የልማት ድጋፍ ሲያደርግ የመጀመሪያው መሆኑን ገልጸዋል።

ድጋፉ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባት በኩል የክልሉን ሥራ የሚያግዝ እንደሆነም ተናግረዋል።

ኃላፊው አማራ ክልል የደረሰውን ውድመት በክልሉ አቅም ብቻ መልሶ ለማቋቋም አስቸጋሪ በመኾኑ ሌሎች ረጅ ድርጅቶችም ተባባሪ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት የክልሉን ጉዳት ተረድቶ ለመደገፍ በመምጣቱም ምስጋና አቅርበዋል።

የልማት ድርጅቱ ዋና ተጠሪ ቱርሃን ሳለህ በበኩላቸው በአማራ ክልል በጦርነት ምክንያት ብዙ የሕዝብ መገልገያ መሰረተ ልማቶች መውደማቸውን እንደተገነዘቡ ገልጸዋል። ይህንን መልሶ ለመገንባትና ለሕዝብ አገልግሎት ለማዋልም የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት ከአማራ ክልል መንግሥት ጋር በመተባበር ይሠራል ብለዋል።

ቱርሃን በአማራ ክልል በጦርነት ውስጥ በነበሩ ዞኖች የሚገኙ ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ የጤና ተቋማ እንዲሁም የፍትሕና የፀጥታ ተቋማት ወድመዋል ብለዋል። የፍትሕ ተቋማትን ሥራ በመደገፍ ክልሉ ሰላሙ የተረጋገጠ እንዲሆን በጋራ እንደሚሠሩም ነው ያስገነዘቡት።

ቱርሃን በጦርነት ምክንያት አነስተኛ የንግድ ሥራቸው የተቋረጠባቸውና ሥራ አጥ ዜጎችን እንደሚደግፉም ተናግረዋል ሲል የዘገበው አሚኮ።

ዛሬ የተደረገው ድጋፍም 14 የመስክ ተሽከርካሪ፣ ጥሬ ገንዘብ እና ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች የተካተቱበት ሲሆን አጠቃላይ የድጋፉ ስምምነት መጠኑም በገንዘብ ሲተመን 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ነው።