“ስለ ኢትዮጵያ” የፎቶግራፍ አውደ ርዕይና ፓናል ውይይት በአርባምንጭ ተከፈተ

“ስለ ኢትዮጵያ” የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ

ሰኔ 21/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያዘጋጀው 5ኛው “ስለ ኢትዮጵያ” የፎቶግራፍ አውደ ርዕይና የፓናል ውይይት በዛሬው እለት በአርባምንጭ ከተማ ተከፍቷል።

የፎቶግራፍ አውደ ርዕይና የፓናል ውይይቱ በደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፣ በአርሶ አደሮች እና በእናቶች ተከፍቷል።

እንግዶቹ የተዘጋጀውን የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ የጎበኙ ሲሆን ትኩረቱን በፌዴራሊዝም ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።

በፎቶግራፍ አውደ ርዕዩ ከ1950ዎቹ እና 60ዎቹ ጊዜያት አንስቶ በየዘመኑ የነበሩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወሳኝ ሁነቶች፣ በታሪክ አንጓዎች የተከሰቱ የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲሁም ለሀገር ሉዓላዊነት የተከፈሉ መስዋዕትነቶችና ከኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ጉዞ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አንኳር ሀገራዊ ክንውኖችን የሚያሳዩ ፎቶግራፎች ለዕይታ ቀርበዋል።

በ12 ከተሞች የሚዘጋጀው የፎቶግራፍ አውደ ርዕዩና የፓናል ውይይቱ በቀጣይም በተለያዩ ከተሞች እንደሚካሄድ ይጠበቃል ሲል ኢፕድ ዘግቧል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW