ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተሽከርካሪዎችን የሚያመርቱ ሀገር-በቀል ኢንዱስትሪዎች እየተፈጠሩ መሆናቸው ተገለጸ

ሰኔ 21/2014 (ዋልታ) አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥማቸውን መሰናክል ተቋቁመው በማለፍ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተሽከርካሪዎች የሚያመርቱ ሀገር-በቀል ኢንዱስትሪዎች እየተፈጠሩ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

ከ100 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረውን “ፍራንኩን ኢት አውቶሞቲቭ” የተባለ ሀገር በቀል የተሽከርካሪ ድርጅት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩና ከፍተኛ አመራሮች ጎብኝተዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በጉብኝታቸው ወቅት እንዳሉት አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥማቸውን መሰናክል ተቋቁመው በማለፍ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተሽከርካሪዎችን የማምረት አቅም ያላቸው ሀገር በቀል ኢንዱስትሪዎች እየተፈጠሩ ናቸው፡፡

አምራች ኢንዱስትሪዎች ከታች ጀምሮ ለሚገጥሟቸው ችግሮች እጅ ከመስጠት ይልቅ ታግለው በማለፍና ለችግሩ መፍትሄ በመፈለግ ለነገ ተስፋ ሰጪና ሀገርን የሚወክሉ ጥራት ያላቸው ምርቶች ማምረት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የድርጅቱ ምርቶች በአሁኑ ጊዜ ያለውን ከፍተኛ የገበያ ፍላጎት ለማርካት በጥራትና በፍጥነት የማምረት አቅምን አሟጦ መጠቀም ይገባል፤ ለዚህም ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርግላቸዋል ብለዋል፡፡

ከፍተኛ አመራሮቹም ከድርጅቱ ባለቤትና ሰራተኞች ጋርም የተወያዩ ሲሆን በውይይቱ የድርጅቱ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ፍራንችስኮ ቪሎኒ ድርጅቱ ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርባቸው መኪናዎች የሀገሪቱን የመንገድ ነባራዊና ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን ያገናዘበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም እስካሁን ወደ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን እንዲሁም ኡጋንዳ ሀገራት ተሽከርካሪዎች ኤክስፖርት መደረጋቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡