ትምህርት የዜጎችን ሁለንተናዊ አቅም የመለወጥ ሚናው የጎላ መሆኑን ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ገለጹ

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ሰኔ 22/2014 (ዋልታ) ትምህርት የዜጎችን ሁለንተናዊ አቅም የመለወጥ ሚናው የጎላ መሆኑን ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ኢትዮጵያን በመወከል በፓሪስ እየተካሄደ ባለው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የትምህርት ቅድመ-ጉባኤ ላይ ተገኝተዋል፡፡

በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ በሚደረገው በዚህ ጉባኤ ላይ ፕሬዝዳንቷ ባደረጉት ንግግር ትምህርት የዜጎችን ሁለንተናዊ አቅም የመለወጥ ሚናው የጎላ መሆኑን አንስተው ለዓለም አቀፍ ዜግነት፣ ለሰላም እና ለሁሉን አቀፍ ማኅበረሰብ የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ከፍ ለማድረግ ትምህርትን የበለጠ ማሻሻል አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የዓለም የትምህርት የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ጥናት እንዲያደርግ በዩኔስኮ የተቋቋመው ዓለም አቀፍ ኮሚሽን ሊቀመንበር ናቸው።

በጉባኤው የ154 ሀገራት የትምህርት ሚኒስትሮች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ፓሪስ ከሚገኘው የፈረንሳይ ኤምባሴ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ቅድመ-ጉባኤው የፊታችን መስከረም ወር በኒውዮርክ ለሚካሄደው የትምህርት ማሻሻል ጉባኤ አስፈላጊውን ዝግጅት ለማድረግ ያለመ መሆኑም ተገልጿል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW