በአዲስ አበባ የሸገር ድጋፍ ሰጪ አውቶብሶች ውል ለተጨማሪ ስድስት ወራት ተራዘመ

የሸገር ድጋፍ ሰጪ አውቶብሶች

ሰኔ 22/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ የሸገር ድጋፍ ሰጪ አውቶብሶችን ውል ለተጨማሪ ስድስት ወራት ማራዘሙን አስታወቀ፡፡

ውሉ ከመጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም እስከ መስከረም 2 ቀን 2015 ዓ.ም መራዘሙ የተገለጸ ሲሆን በመዲናዋ ድጋፍ ሰጪ አውቶቡሶች ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ በየቀኑ አገልግሎት እንዲሰጡ በመደረጉ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ እንዲሻሻል አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ተገልጿል፡፡

በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት በሸገር የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በኩል ስምሪት እየተሰጣቸው የሚገኙ አውቶብሶች አገልግሎት መስጠታቸውን እንዲቀጥሉ ውላቸው ተራዝሟል ነው የተባለው፡፡

ከቢሮው ያገኘነው መረጃ እንዳመለከተው ማኅበራትም በውሉ መሰረት የተቀመጡ የአሰራር ሥርዓቶችን ሥራ ላይ በማዋል ከዚህ የተሻለ አገልግሎት እንዲኖር ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ መሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

በሁሉም አውቶብሶች ጂፒ ኤስ በመግጠም የክትትልና ቁጥጥር ሥራው የተጠናከረ እና አገልግሎት አሰጣጡም የተሻሻለ እንዲሆን በትኩረት እንዲከወንም ቢሮው አስታውቋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ከጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ሀገር አቋራጭ አውቶብሶች በኪራይ መልክ በመዲናዋ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉ የሚታወስ ነው።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW