የአፍሪካ ኅብረትና ኢጋድ ሀገራቱ በድንበራቸው የተፈጠረውን ውዝግብ በውይይት እንዲፈቱ አሳሰቡ

ሰኔ 22/2014 (ዋልታ) የአፍሪካ ኅብረት እና ኢጋድ ኢትዮጵያ እና ሱዳን በድንበራቸው አካባቢ የተፈጠረውን ውዝግብ በውይይት እንዲፈቱ አሳሰቡ፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ሁለቱም ሀገራት ከወታደራዊ እርምጃ እንዲታቀቡ ማሰሰባቸውን ከኅብረቱ ቲውተር ገጽ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ሀገራት የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ውይይትን እንዲያስቀድሙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ውዝግቡ እየተከሰቱ ያሉ የውስጥ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እየተደረጉ ያሉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ማደናቀፍ እንደሌለበትም ጠቁመዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) በበኩሉ በሀገራቱ መካከል ያለው የድንበር ውዝግብ ውጥረት እንዲረግብ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ጥሪ አቅርቧል።

የኢጋድ ዋና ፀሃፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ሀገራቱ የረጅም ጊዜ የመንድማማችነት ታሪክ እንዳላቸው አንስተው ውጥረቱን የበለጠ ሊያባብሱ ከሚችሉ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ሀገራቱ ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን እንዲከተሉ በአጽንኦት ጠይቀዋል።