የብሔራዊ ስታዲየም የግንባታ ወጪ ዋጋ ማሻሻያ ሊደረግበት መሆኑ ተገለጸ

ሰኔ 22/2014 (ዋልታ) የብሔራዊ ስታዲየም የግንባታ ወጪ ዋጋ ማሻሻያ ሊደረግበት መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ ገለጹ።

በአዲስ አበባ እየተሠራ ያለው ብሔራዊ ስታዲየም /አደይ አበባ ስታዲየም/ በቻይናው ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ግንባታው በመከናወን ላይ ይገኛል።

ግንባታው በታኅሣሥ 2008 ዓ.ም የተጀመረው እና 62 ሺሕ ሰዎችን በወንበር የመያዝ አቅም ያለው ስታዲየሙ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መጠናቀቁ ይታወቃል።

የሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ በ5 ነጥብ 57 ቢሊዮን ብር በሁለት ዓመት ከስድስት ወር ለማጠናቀቅ ታቅዶ በ2012 ዓ.ም ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም እስካሁን 50 በመቶ እንኳን መከናወን አልቻለም።

የዘገየበት ዋና ምክንያት ደግሞ ከክፍያ ሥርዓት ጋር በተፈጠረ ችግር እና በኮሮናቫይረስ መከሰት ሳቢያ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ ተናግረዋል።

በዚህ ሳቢያ የዘገየው ስታዲየሙ የስራ ተቋራጩ (የቻይናው ስቴት ኮንስትራክሽ) የዋጋ ማሻሻያ እንዲደረግ መጠየቁን ገልጸው 40 በመቶ በውጭ ምንዛሬና 60 በመቶ በብር የነበረውን የክፍያ አፈፃፀም ስምምነት እንዲሻሻል መጠየቁንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የዓለም እና የሀገር ውስጥ እቃዎችን መናር ተከትሎ መንግሥት ማሻሻያውን ለማድርግ ዝግጁ ቢሆንም ተቋራጩ የጠየቀው ማሻሻያ ተጋኗል ብለዋል።

የግንባታ ሂደቱ መቀጠሉን የገለጹት ሚኒስትሩ በተቋራጩ የተጠየቀው የዋጋ ማማሻያ ከዚህ በፊት ለተሠራው ጭምር በመሆኑ እስካሁን ስምምነት ላይ አለመደረሱን አስታውሰው ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

በሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ ጣሪያ ማልበስ፣ ወንበር መግጠም፣ የሰው ሠራሽ ሐይቅ ግንባታ፣ ዘመናዊ የደኅንነት ካሜራ መግጠም፣ ሳውንድ ሲስተም መዘርጋት፣ የፓርኪንግ ቦታዎች፣ የተጫዋቾች የመለማመጃ ሜዳ እና ሌሎችም ይገኙበታል።