የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 1 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል እየተዘጋጀ ነው

ሰኔ 24/2014 (ዋልታ) በአገር ዐቀፍ ደረጃ በተጀመረው በ4ኛ ዙር አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 1 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው ባሉት 8 የችግኝ ጣቢያዎች አማካኝነት ነው 1 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው።

ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክተር ተክሉ ወጋየሁ (ዶ/ር) በአራተኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ይተከላሉ ተብለው ከታቀዱ 1 ሚሊዮን ችግኞች ውስጥ 25 ሺሕ የሚሆኑት ችግኞች የሚተከሉት በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አባላት እንደሆነ ተናግረዋል።

ከዚ ቀደም ለሦስት ተከታታይ አመታት በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ውጤት እንደመጣ የገለፁት ዳይሬክተሩ በአሁኑ ክረምቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ሌላው አስተያየታቸውን የሰጡት የዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮ ሃብት አያያዝ ትምህርት ክፍል መምህርና የልማት ሥራዎች አስተባባሪ ይበልጣል ይሁኔ (ረ/ፕ) በ4ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የሚተከሉ ችግኞች በርካታ ጥቅሞች ላይ የሚውሉ እንደሆነ ገልፀዋል።

በክረምቱ የሚተከሉ ችግኞች ለምግብነት፣ ለአካባቢ ጥበቃ ብሎም ለከተማ ውበት የሚያገለግሉ ናቸው ብለዋል።

በሦስት ዙር በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የተተከሉ ችግኞች ከዘጠና በመቶ በላይ መፅደቃቸውንም ጠቁመዋል።

ችግኞችን ከመትከል ባለፈ የመንከባከብ ዘመቻው አሁንም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

ሱራፌል መንግሥቴ (ከአርባ ምንጭ)