ንፁሀንን ኢላማ ያደረገ ጥቃት ሊቆም ይገባል – የህግ ባለሙያዎች

ሰኔ 24/2014 (ዋልታ) ንፁሀንን ኢላማ ያደረገ ጥቃት ሊቆም ይገባል ሲሉ ዋልታ ያነጋገራቸው የህግ ባለሙያዎች ተናገሩ።

እንደ ሸኔና ጋነግ ባሉ የሽብር ቡድኖች አማካኝነት የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ከማውገዝ በዘለለ መንግሥት የሚወስደውን እርምጃ ማጠናከር እንዳለበትም ነው የህግ ባለሙያዎቹ የገለፁት።

መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ማስከበር አለበት ያሉት የህግ ባለሙያው ጎድሴንድ ኮኖፋ ከሰሞኑ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተፈፀሙ ጥቃቶች ከህግ አንፃር ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ችግሮች ሲፈጠሩ ከማውገዝ በዘለለ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠትና እርምጃ ለመውሰድ መንግሥት ቁርጠኛ መሆን እንዳለበትም ነው የተናገሩት።

ኅብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላምና ደኅንነት በመጠበቁ ረገድ ከመንግሥት ጋር ተባብሮ መስራት ይኖርበታልም ነው ያሉት የህግ ባለሙያው።

ንፁሀን ዜጎችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት እንደሌለው የገለፁት ሌላኛው የህግ ባለሙያ ዳግም ወንድሙ መንግሥት የዜጎቹን ደኅንነት ማስጠበቅ እንዳለበት ጠቁመዋል።

የሽብር ቡድኖቹ በተለያየ ጊዜያት የሚፈፅሙትን ድርጊት ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባውም ነው የተናገሩት።

ኅብረተሰቡም የአካባቢውን ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቁ ሂደት ላይ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲሉ የህግ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።

በሱራፌል መንግሥቴ (ከአርባ ምንጭ)