የቦንጋ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ 856 ዕጩ መምህራንን አስመረቀ

ሰኔ 25/2014 (ዋልታ) የቦንጋ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በመደበኛ መርኃ ግብር ያሰለጠናቸውን 856 ዕጩ መምህራን አስመርቋል።

የኮሌጁ ዲን አንተነህ አየለ ኮሌጁ ዕጩ መምህራንን አሰልጥኖ ሲያስመርቅ ለ23ኛ ጊዜ መሆኑን ጠቁመው በዛሬው እለትም በ20 የትምህርት መስኮች 483 ወንዶችና 373 ሴት በድምሩ 856 ዕጩ መምህራንን ማስመረቁን ገልጸዋል።

ኮሌጁ በሰርትፍኬት ደረጃ ለማሰልጠን ከተመሰረተበት ከ1991 ዓ.ም እስከ 2013 ዓ.ም በመደበኛና በተከታታይ የስልጠና መርኃ ግብሮች ከ38 ሺሕ 631 በላይ መምህራንን በማሰልጠን ወደ መምህርነት ሙያ አሰማርቷል ብለዋል።

አክለውም በትምህርትና በመልካም ሥነ-ምግባር የታነፀ ራሱንና ማንነቱን በውል የተገነዘበ ትውልድ ካልተገነባ ወደፊት እንዲኖረን የምንፈልጋት ሀገር ሊትኖረን አትችልም ሲሉ ተናግረዋል።

ተመራቂዎች ወደ መምህርነት ሙያው በሚሰማሩበት ወቅትም ሀገርና ሕዝብ የጣለባቸውን ትውልድን የማነፅና የመቅረፅ ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡም አሳስበዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አልማው ዘውዴ በበኩላቸው ሀገሪቱ የጀመረችውን የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት የተማረ ዜጋ ማፍራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ስለሆነም የዛሬ ተመራቂ ተማሪዎች በተማሩበት የሙያ መስክ በታማኝነትና በቅንነት እንዲያገለግሉ መጠየቃቸውን ኮሌጁ የላከልን መረጃ አመላክቷል።