ኮሚሸኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አጠናቅቆ ወደ ዝግጅት ምዕራፍ መግባቱን አስታወቀ

ሰኔ 26/2014 (ዋልታ) የአገራዊ ምክክር ኮሚሸን የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎችን አጠናቅቆ ወደ ዝግጅት ምዕራፍ መግባቱን የኮሚሽኑ ሰብሳቢ መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ገለጹ።
ኮሚሽኑ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ተቋቁሞ የኮሚሽኑ ሰብሳቢና አመራሮች ከተሾሙለት በኋላ በይፋ ወደ ቅድመ ዝግጅት ሥራ መግባቱ ይታወቃል።
በዚህም ኮሚሽኑ ከመንግሥት ኃላፊዎች፣ ከክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ትውውቅ አድርጓል።
በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ኮሚሽኑን የማደራጀት ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን የድርጊት መርኃ ግብር በማውጣትም ወደ ዝግጅት ምዕራፍ የሚያስገቡ ሥራዎችን አከናውኗል።
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አጠናቆ ወደ ዝግጅት ምዕራፍ መግባቱን ተናግረዋል።
በዝግጅት ምዕራፉም ለሥራ የሚያስፈልገውን በጀትና ስትራቴጂክ እቅድ ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ ሲሆን በአጭር ጊዜ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አጸድቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
በዚሁ ምዕራፍ በአገራዊ ምክክሩ ሂደት የሚዘጋጁ የውይይት መድረኮችን የሚመሩና የሚያወያዩ ግለሰቦችንና ባለድርሻ አካላትን የመምረጥና ስልጠና የመስጠት ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቅሰዋል።
በዚህም መሰረት ስለአገራዊ ምክክሩ ከአወያዮችና ተወያዮች ጋር በሚሰሩ ተግባራት ዙሪያ መግባባት ላይ በመድረስ ወደ ምክክር የሚገባበትን ምቹ መደላድል እንደሚፈጠር ነው የተናገሩት።
የዝግጅት ምዕራፉ በሚቀጥለው ዓመት የመጀመሪያ ወራት ሊጠናቀቅ እንደሚችል የጠቆሙት የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ዝግጅቱ እንደተጠናቀቀም በተመረጡ አጀንዳዎች ላይ ውይይትና ምክክር እንደሚኖር አመልክተዋል።
ኢትዮጵያውያን በውይይት ችግሮቻቸውን በማስወገድ ለቀጣዩ ትውልድ መልካም ውርስን ማስተላለፍ አለባቸው ብለዋል።
በአገሪቱ የዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባት እንዲረጋገጥና ሰላም እንዲሰፍን የጥይቶች ጩኸቶችን በማቆም ሁሉም ወደ ወይይት መግባት አለበት ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል