4ኛው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በደብረ ብርሃን ከተማ ተጀመረ

ሰኔ 27/2014 (ዋልታ) “በጎነት ለኢትዮጵያዊነት ከፍታ” በሚል መሪ ሀሳብ 4ኛው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በደብረ ብርሃን ከተማ ተጀመረ፡፡
በብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ከ6 ሚሊየን በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበት የ2014 የክረምት በጎ ፍቃድ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር በደብረ ብርሃን ከተማ አስጀምሯል፡፡
ወጣቶች በአረንጓዴ ልማት ላይ አሻራቸውን ሲያሳርፉ የለመለመችና ለዜጎቿ ምቹ የሆነች ሀገር ለትውልዱ ከማስረከባቸው ባለፈ በጀግኖች እናቶችና አባቶች በከፍተኛ መስዋእትነት የተረከቧትን ታላቅ ሀገር ታሳቢ በማድረግ በውስጥም በውጭም የሚጋረጡብንን ፈተና በአንድነት መንፈስ ለመመከት እና ሀገርን ለማስከበር የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነው ሲሉ የከተማዋ ተቀዳሚ ከንቲባ ካሳሁን እምቢአለ ተናግረዋል።
ወጣቶች ለሀገር ልማት ግንባር ቀደም መሆናቸውን ያነሱት ተቀዳሚ ከንቲባው ከጊዜ ወደ ጊዜ የሀገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ የፀረ ሰላም ኃይሎችን እኩይ ተግባር ለማክሸፍ ወጣቶች ለሀገራቸው ኅልውና አንድ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡
የብልፅግና ወጣቶች ሊግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባን ጨምሮ የወጣቶች ሊግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባና ደም ልነሳ እንዲሁም በከተማዋ የተከናወኑ የግብርና እንቅስቃሴዎች ጉብኝት እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡
በመድረኩ የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አለሙ ስሜን (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ከሁሉም ክልል የተወጣጡ ወጣቶች ታድመዋል፡፡
አመለወርቅ መኳንንት (ከደብረ ብርሃን)