በአማራ ክልል የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ከነገ ጀምሮ ይሰጣል

ሰኔ 27/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ከነገ ጀምሮ እንደሚሰጥ ተገለጸ፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2014 ዓ.ም የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና አሠጣጥን አስመልክቶ መግለጫ ሠጥቷል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሙላው አበበ የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ለመስጠት የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን ገልጸው ፈተናውም ከሰኔ 28 እስከ 30/2014 ዓ.ም ይሠጣል ብለዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በመደበኛ፣ በማታ እና በግል የስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ለተከታተሉ ከ359 ሺሕ በላይ ተማሪዎች በ5 ሺሕ 395 ትምህርት ቤቶች ላይ ክልላዊ ፈተና እንደሚወስዱም ገልጸዋል።

ፈተናውን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ከ10 ሺሕ በላይ መምህራን እንደሚሳተፉና የጸጥታ ችግር እንዳይከሰት የጸጥታ አካላት ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ተማሪዎች ፈተናውን በተረጋጋ እና ሥነምግባር በተሞላበት ሁኔታ እንዲፈተኑ መምህራን፣ ወላጆች እና የጸጥታ አካላት ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

በፈተና ወቅት ኩረጃ ሊያስከትል የሚችለውን ቅጣት በተዘጋጀው የፈተና ማስፈጸሚያ መመሪያ ላይ አብሮ የወረደ በመሆኑ ተማሪዎች ወደ ቅጣት እንዳይገቡ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

የወላጅ መምህር ኅብረት አባላት ፈተናው ታሽጎ ፈተና ጣቢያው ላይ መድረሱን እና በተማሪዎች ፊት መከፈቱን ማረጋገጥ እንደሚገባቸውና የፈተና ጣቢያ ኃላፊዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ማሳሰቡን የአሚኮ ዘገባ ያመለክታል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW