ምክትል ጠ/ሚ ደመቀ ተጨማሪ ጥቃትና ጭፍጨፋ እንዳይከሰት የሚሊሻ እና የኮሙኒቲ ፖሊሲንግ ስርዓት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል አሉ

ሰኔ 28/2014 (ዋልታ) በወገኖቻችን ላይ ተጨማሪ ጥቃትና ጭፍጨፋ እንዳይከሰት በሁሉም አካባቢዎች ተጋላጭ ቀበሌዎች እና መንደሮችን በመለየት አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግላቸው እንዲሁም ነዋሪው ራሱን በተደራጀ መልኩ እንዲከላከል የሚሊሻ እና የኮሙኒቲ ፖሊሲንግ ስርዓት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

በወለጋ አካባቢ አሁንም አሸባሪው የሸኔ ቡድን በንፁሃን ወገኖቻችን ላይ አሳዛኝ ጭፍጨፋ ማካሄዱን ገልጸው፤ “ጥቃቱ የአማራ ብሄር ተወላጆችን ዒላማ ያደረገና ተጠቂዎችን ለመከላከል ሙከራ ባደረጉ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ጭምር ያነጣጠረ ነው” ብለዋል።

ይህ ቡድን ህፃናትን፣ እናቶችን እና ደካማ አረጋውያንን ለይቶ ተደጋጋሚ ጥፋት በመፈፀም ሀገር የማፍረስ ግልፅ ተልዕኮ ያነገበ የተስፋ ቢሶች ጥርቅም መሆኑን በተግባር አረጋግጧል ሲሉ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።

መንግሥት በመላው ሀገሪቱ በተለይም ተደጋጋሚ ጥቃት በሚፈፀምባቸው አካባቢዎች ህግ ለማስከበር፣ ሰላም እና ፀጥታ ለማስፈን እንዲሁም ዜጎች የተረጋጋ ህይወት እንዲመሩ ለማስቻል ጠንካራ ርብርብ እያደረገ ቢሆንም፤ አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች አሸባሪ ቡድኑ በንፁሃን ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ጥፋት መፈፀሙን ቀጥሏል ብለዋል።

በማንኛውም መመዘኛ ድርጊቱ በፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ቅንብር እየተፈፀመ ያለ ኢ-ሰብዓዊ እና ዘግናኝ በመሆኑ፤ መንግስት ከአካባቢው ሕዝብ ጋር በመተባበር የጀመረውን ህግ የማስከበር እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

“በወገኖቻችን ላይ ተጨማሪ ጥቃትና ጭፍጨፋ እንዳይከሰትም በሁሉም አካባቢዎች ተጋላጭ ቀበሌዎች እና መንደሮችን በመለየት አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግላቸው እንዲሁም ነዋሪው ራሱን በተደራጀ መልኩ እንዲከላከል የሚሊሻ እና የኮሙኒቲ ፖሊሲንግ ስርዓት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል” ሲሉ ችግሩን ለመከላከል እንደሚሰራ አመልክተዋል።

በመልዕክታቸው ጨረሻም “ህብረታዊ የትግል እንቅስቃሴያችን እንዲከሽፍ ጠላት አስልቶ በርቀት የሚጠባበቀው የሴራ ውጤት በመሆኑ፤ በተደጋጋሚ በደረሰብን ጥፋት ሳንንበረከክ አንድነታችንን አጥብቀን በፅናት እንድንጓዝ አደራ እያልኩ በተጎጂ ወገኖች የተሰማኝን ልባዊ ሀዘን እገልፃለሁ” ብለዋል።