በብዙ ውጣ-ውረድ ታጅበን ትልቅ ውጤት ማስመዝገብ ችለናል – አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ

አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ

ሰኔ 28/2014 (ዋልታ) በብዙ ውጣ-ውረድ ታጅበንም ቢሆን ትልቅ ውጤት ማስመዝገብ ችለናል ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ የምክር ቤቱን የአፈጻጸም ደረጃ አመላከቱ፡፡

የምክር ቤቱ አማካሪ እና አስተባባሪ ኮሚቴዎች እንዲሁም የመንግሥት ዋና እና ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታዎች በተገኙበት የአሥራ አንዱም የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የ2014 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ተገምግሟል፡፡

አፈ ጉባዔ ታገሠ በዚሁ ወቅት ከመንግሥት ምስረታ ጊዜ ጀምሮ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማሳተፍ ምክር ቤቱ ለሀገር ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አንስተዋል፡፡

እንደ ሀገርና እንደ ተቋም የተሠሩ ሥራዎች አበረታች እንደሆኑ እና በቋሚ ኮሚቴዎች የቀረቡት ተጨማሪ ሀሳቦች አስተማሪ እንደሚሆኑ ነው ያመለከቱት።

ስለሆነም ቆም ብለን በማሰብ፣ ሀገራችንን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ፣ የሁላችንም ቀና ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ በበኩላቸው ጥሩ የሠሩ ተቋማት የሚበረታቱበት፣ ያልሠሩት ደግሞ የሚጠየቁበት የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ በልጅጌ በምክር ቤቱ መሻሻሎች እንዳሉ አንስተው የምክር ቤቱ አባላት ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የክትትልና ቁጥጥር ሥራቸውን ምክር ቤቱን በሚመጥን ደረጃ ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴዎች አመራሮች እና አባላት በሕዝቦች ዘንድ በሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች፣ በሙስና፣ በብልሹ አሠራሮች ላይ ግልጸኝነትን እና ተጠያቂነትን እያረጋገጡ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል፡፡

የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ምሕረቱ ሻንቆ በበኩላቸው የምክር ቤቱ ዋና ተግባር በሕገ-መንግሥቱ የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት መወጣት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአሥራ አንዱም የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች በክትትል እና ቁጥጥር፣ በሕግ አወጣጥ፣ በፓርላማ ዲፕሎማሲ እና በሕዝብ ውክልና ሥራዎች ምክር ቤቱ በተሰጠው ስልጣን እና ኃላፊነት መሠረት የ2014 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጻም ሪፖርታቸውን አቅርበዋል፡፡

በመሠረተ ልማቶች፣ በሕንጻ ግንባታዎች፣ በዜጎች ፍትሐዊ የቤት ተጠቃሚነት፣ በትራንስፖርት፣ በመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች፣ እያንዳንዱ ቋሚ ኮሚቴ በሚከታተላቸው ተቋማት በውጤት የተመሠረቱ ሥራዎችን በመሥራት የሕዝብን ጥያቄዎች መመለስ እንዳለበትም የምክር ቤቱ አማካሪ ኮሚቴ አባላት ማስገንዘባቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW