የሱዳኑ ወታደራዊ መሪ ሥልጣን ለመልቀቅ ፈቃደኛ መሆናቸውን ገለጹ

ሰኔ 28/2014 (ዋልታ) የሱዳን ጦር ኃይል አገሪቱ ወደ ሲቪል አስተዳደር እንድትመለስ ለማድረግ ቦታውን እንደሚለቅ ወታደራዊው መሪ ጄኔራል አብዱል ፋታህ አል-ቡርሃን ተናገሩ።

የአገሪቱ ጦር ኃይል ሱዳን ወደ ዴሞክራሲ ለምታደርገው ሽግግር እንቅፋት እንደማይሆንና ምርጫ እንዲደረግ ወስኖ እየሠራ እንደሆነ ገልጸዋል።

ጄኔራል አል-ቡርሃን ጨምረውም በአገሪቱ ያለውን ፖለቲካዊ ቀውስ ለማብቃት ከሲቪል ቡድኖች ጋር በሚደረገው ድርድር ላይ ጦር ሠራዊቱ የሚያደርገውን ተሳትፎ እንደሚያቋርጥ አሳውቀዋል።

ነገር ግን አገሪቱ ውስጥ ምርጫ ስለሚደረግበት እንዲሁም ጦር ኃይሉ ሥልጣን ስለሚያስረክብበት ሂደት የጊዜ ሰሌዳ ምንም አለማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በሱዳን ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመሰረት የሚጠይቁት ተቃዋሚ ሰልፈኞች ሠራዊቱ ከፖለቲካው እንዲወጣ በመጠየቅ ለወራት የዘለቀ ተቃውሞ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል።

ይህ የአሁኑ የጄኔራሉ ውሳኔም ከሕዝቡ በገጠማቸው ተከታታይ ተቃውሞ የሰጡት ወሳኝ ምላሽ እንደሆነ ተነግሯል። በመላው አገሪቱ ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ ግዙፍ ሕዝባዊ ሰልፎች እየተካሄዱ ይገኛሉ።

የሽግግር መንግሥቱ አካል የነበሩት የሱዳን ጦር ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች ባለፈው ጥቅምት ወር በሲቪሉ የሽግግር መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ላይ መፈንቅለ መንግሥት ፈጽመው ነበር ሥልጣን የተቆጣጠሩት።

የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ የሆኑት ጄኔራል አል-ቡርሃን ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ በአገሪቱ ወደ ዴሞክራሲ የተጀመረውን የሽግግር ሂደትን በመቀልበስ መሪነቱን ጨብጠው ቆይተዋል፡፡