ፓርላማው ነገ ጠ/ሚ ዐቢይ በተገኙበት በአዲሱ የ2015 በጀት ድልድል ላይ ይወያያል

ሰኔ 29/2014(ዋልታ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች 6ኛው ምክር ቤት በ1ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ በሚያካሂደው 16ኛ መደበኛ ጉባዔ፤ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በነገው ዕለት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ይወያያል።

ፓርላማው በዚህ መደበኛ ጉባዔው፤ ሰሞኑን በተደጋጋሚ እየተከሰተ ላለው የዜጎች የፀጥታ እና ደኅንነት ጉዳይ ዐቢይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚወያይ ይጠበቃል።

እንደዚሁም ለሌሎች ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ-ሀብታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ትኩረት ተሰጥቶ፤ ምክር ቤታዊ ውይይት ይካሄዳል።

በተጨማሪም በአዲሱ የ2015 የበጀት ድልድል ላይ ተወያይቶ እንደሚያጸድቀውም ተመላክቷል፡፡

የፌዴራል መንግስት አጠቃላይ ዓመታዊ የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትም የሚቀርብ ሲሆን፣ በዚሁ ሪፖርት ላይም ምክር ቤቱ ከጠቅላይ ሚኒሰትሩ ጋር እንደሚወያይ ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።