በአሸባሪው ሸኔ ላይ በተወሰደው እርምጃ የምዕራብ ወለጋ ዞን ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሰ መሆኑ ተገለጸ

ዋና አዛዥ ኮማንደር ነገራ ዱፌራ

ሐምሌ 4/2014 (ዋልታ) በአሸባሪው ሸኔ ላይ በተወሰደው ጠንካራ እርምጃ የምዕራብ ወለጋ ዞን ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሰ መሆኑን በኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የምዕራብ ወለጋ ዞን ልዩ ኃይል ዋና አዛዥ ኮማንደር ነገራ ዱፌራ ገለጹ።

በአሸባሪው ሸኔ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ዋና አዛዡ አረጋግጠዋል።

አሸባሪው በደረሰበት ከባድ ምት በሽሽት ላይ እያለ በቶሌ ቀበሌ በንጹኃን ዜጎች ላይ ጭካኔ የታከለበት ጭፍጨፋ መፈጸሙን አስታውሰው በተወሰደበት እርምጃ ዘርፎ የወሰዳቸው ንብረቶች እየተመለሱ መሆኑን ገልጸዋል።

የጸጥታ ኃይሉ የአካባቢው መልክአ ምድር ሆነ የአየር ንብረት ተጽዕኖ ሳይበግረው የሽብር ቡድኑን ለማጥፋት ሌት ተቀን እየተሰራ መሆኑንም ኮማንደር ነገራ ዱፌራ ጠቅሰዋል።

በመከላከያ ሰራዊትና በክልሉ የጸጥታ ኃይል የተቀናጀ እርምጃ የምዕራብ ወለጋ ዞን ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሰ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑን በማጥፋት በሕዝብ ላይ ድጋሚ ጥቃት እንዳያደርስ ለማድረግ የጸጥታ ኃይሉ በቁርጠኝነት እየሰራ የገለጹት ዋና አዛዡ የጸጥታ ኃይሉ የሕዝብን ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ የሽብር ቡድኑ ይንቀሳቀስባቸው በነበሩ አካባቢዎች ሁሉ የተቀናጀ የኦፕሬሽን ሥራ ላይ ይገኛል ብለዋል።

እየተካሄደ በሚገኘው ህግና ሥርዓትን የማስከበር ተግባር አሸባሪው ሸኔ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ እንዳጋጠመው ጠቁመዋል።

በአሸባሪ ቡድኑ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ኮማንደር ነገራ ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW