ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ ምርጫ ሳይሆን ሀገር የመገንባት ጉዳይ መሆኑ ተገለጸ

ሐምሌ 4/2014 (ዋልታ) ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ ምርጫ ሳይሆን ሀገር የመገንባት ጉዳይ ነው ሲሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ገለጹ፡፡

ምክር ቤቱ ከዴሞክራሲ ተቋማት ጋር እያካሄደ በሚገኘው የጋራ ፎረም ላይ የመንግስት ዋና ተጠሪው አቶ ተስፋዬ  በሰጡት አስተያየት፤ የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ የዴሞክራሲ ባሕል ግንባታ ስራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማትን ለመገንባት የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

ለአብነትም በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና በዕንባ ጠባቂ ተቋም በኩል ለውጥ ለማምጣት ታልመው የተከናወኑት ሥራዎች አበረታች ናቸው ብለዋል፡፡

የሰብዓዊ መብት እና የዕንባ ጠባቂ ተቋም የሪፎርም ሥራዎች አተገባበር እና ተቋማቱን ለማጠናከር የተሠሩ ስራዎች እንዲሁም ጥንካሬ እና ድክመቶች ተለይተው ለጋራ ፎረሙ መቅረባቸውንም የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡