“ሸኔ እና ትሕነግ መጠነ ሰፊ ጥፋት እየፈፀሙብን ነው” – ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ

ሐምሌ 05/2014 (ዋልታ) አሸባሪዎቹ ሸኔ እና ትሕነግ በአማራ ሕዝብ ላይ መጠነ ሰፊ ጥፋት እየፈጸሙ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ይህንን ያሉት ከሰሜን ሸዋ ዞን የኅብረተሰብ ተወካዮች ጋር ዛሬ በደብረ ብርሃን ከተማ እየተወያዩ ባሉበት ወቅት ነው።

በውይይቱ ላይ ርዕሰ መስተዳድሩ የአማራ ሕዝብ እንደ ሕዝብ በርካታ ጥቃቶች እየተፈፀመበት ነው ያሉ ሲሆን ጥቃቱን ማክሸፍ የሚቻለው በመደማመጥና በመተባበር ብቻ ነው ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት ከውስጥም ከውጭም እየደረሱ ያሉ ጫናዎችን ለመቋቋም በሰከነ መንገድ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ያወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ “ሸኔ እና ትሕነግ መጠነ ሰፊ ጥፋት እየፈፀሙብን ነው” ብለዋል፡፡

ይህን መጠነ ሰፊ ጥቃትና ጥፋት የሚያቀናብሩትንና በክልሉ ውስጥም ከክልሉ ውጭም ባሉ አካባቢዎች እያደረሱት ያለውን የጥፋት አጀንዳ ለማክሸፍ ጠንካራ መንግሥታዊ መዋቅር መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ የክልሉ መንግሥት ይህንን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት እየሠራን ነው ብለዋል።

በክልሉ ውስጥ ለአብነት ከሰሞኑ በአጣዬና አካባቢው የደረሰው ጥቃት በተደጋጋሚ ረፍት ለመንሳት የሽብር ቡድኖች የጠነሰሱልን ሴራ አካል ነው ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።

በተለያዩ አካባቢዎች በሚደርሱ ጥፋቶች ሁሉ የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ ሀዘን እንደሚሰማው የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ የዚህ ሁሉ ችግር ማሰሪያው ሰከን ባለ መንገድ ስር የሰደዱ ችግሮችን ለመፍታት ተደማምጦ መሥራት በመሆኑ ለዚህ ተግባራዊነት ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በአማራ ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት የመጀመሪያ ተጎጅ አማራውን ያድርግ እንጅ የመላው ኢትዮጵያውያን ጥቃት መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እየደረሰ ያለውን ጥፋት በቃ ሊል ይገባል ብለዋል።