የሥራ ዕድል ፈጠራና የሙያ ደኅንነት ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተደረገ


ሐምሌ 5/2014 (ዋልታ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና የቱሪዝም ሚኒስቴር በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

የሰው ኃይል እና የቴክኖሎጂ ልማት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና የሥራ ፈጣሪነት አስተሳሰብ እንዲሁም የሙያ ደኅንነትና ጤንነት ሚኒስቴሮቹ በጋራ ለመስራት የተስማሙባቸው የትብብር የትኩረት መስኮች ናቸው፡፡

የሥና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በወቅቱ እንደገለፁት ስምምነቱ ሥራውን በላቀ ደረጃ ተቋማዊ መልክ እንዲይዝና እና ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ያለመ ነው፡፡

የሁለቱ ተቋማት ትብብር በቂ የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማቅረብና የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የቱሪዝም ዘርፉ በኢኮኖሚ እድገት ያለውን ሚና በብቃት እንዲወጣ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በቱሪዝም ሀብት እጅግ የታደለች ሀገር ብትሆንም አልምቶ መጠቀም ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡

ስምምነቱ የአግልግሎት ጥራትና ደረጃ ከማሻሻል፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የቱሪዝም ክፍለ ኢኮኖሚ ኢንዱስትሪው ከሀገር ባለፈ ለውጪ ገበያ አስተዋጽኦ እንዲኖረው እንደሚያደርግ መግለጻቸውን ከሥና ክህሎት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡