ዋልታን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ከ30 ሺሕ በላይ ችግኞችን በሞጆ ተከሉ

ሐምሌ 5/ 2014 (ዋልታ) የመገናኛ ብዙኃን ፣ የጸጥታ እና የትራንስፖርት ተቋማት በአንድ ጀንበር ከ30 ሺሕ በላይ ችግኞችን በሞጆ ከተማ ተከሉ፡፡

የችግኝ ተከላ መርኃ ግብሩን በጋር ያከናወኑት ተቋማት ዋልታ ሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ፣ ፌደራል ፖሊስ፣ ማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ሎጅስቲክ አገልግሎት ድርጅት ሲሆኑ በከ30 ሺሕ በላይ የፍራፍሬ እና የጫካ ደን ችግኞችን ዛሬ በሞጆ ከተማ አካባቢ ተክለዋል፡፡

የእለቱን ፕሮግራም ያስተባበረው የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ሎጅስቲክ አገልግሎት ድርጅት ሥራ አስፈፃሚ ሮባ መገርሳ ድርጅታቸው በመንግሥት ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠውን አረንጓዴ አሻራ ልማት መርኃ ግብር ከፍተኛ ተሳትፎ ያደረገ መሆኑን ገልጸው ድርጅታቸው ከሎሜ ወረዳ በተሰጠ 14 ነጥብ 5 ሄክታር ጥብቅ መሬት ላይ ባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት 28 ሺሕ 750 የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ችግኞች የድርጅቱ ሰራተኞች እና አጋር አካላት በማሳተፍ መትከላቸውን አስታውሰዋል፡፡

የተቋማቱ ሰራተኞች ከዚህ ቀደም በተካሄዱ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብሮች ላይ መሳተፋቸዉ የተገለፀ ሲሆን ዘንድሮም በ4ኛው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ላይ በመሳተፍ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡

የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር በሀገሪቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለፁት የተቋማቱ ሰራተኞች ችግኞቹ በሚተከሉበት ልክ እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል፡፡

ዜጎች በአረንጓዴ ልማት ላይ አሻራቸውን ሲያሳርፉ የለመለመችና ለዜጎቿ ምቹ የሆነች ሀገርን ለቀጣዩ ትውልድ ያስተላልፋሉ ሲሉም አክለዋል፡፡

አረንጓዴን የተላበሰችና ለዜጎቿ ምቹ የሆነች ሀገርን ለመገንባት ደግሞ ችግኞችን ከመትከል ባሻገር መንከባከብ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ በአጽኖት ገልጸዋል፡፡

አመለወርቅ መኳንንት (ከሞጆ)