ለተማሪ ቢንያም ኢሳያስ “ባችለር ኦፍ ባዮሜዲካል ሳይንስ” ሊሰጠው እንደሆነ የህክምና ኮሌጁ ገለፀ

ሐምሌ 5/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ሲከታተል ቆይቶ ትምህርቱን እንዲቋርጥ የተደረገው ተማሪ ቢንያም ኢሳያስ ተጨማሪ ትምህርት ሳይማር ባችለር ኦፍ ባዮሜዲካል ሳይንስ ሊሰጠው መወሰኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ገለፀ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ተማሪውን በሚመለከት የወሰነውን ውሳኔ አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የጤና ሳይንስ ኮሌጁ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶክተር አንዷለም ደነቀ እንደገለፁት ተማሪ ቢኒያም ኢሳያስ አራተኛ አመት ተማሪ እያለ ነው የአካል ጉዳት እንዳለበት የታወቀው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ላለፉት ስምንት ወራት ጉዳዩን ይዞ ሲመረምር ቆይቷል፡፡

ባዋቀረው ኮሚቴ በቀረበለት ምክረ ሀሳብ መሰረት ተማሪ ቢንያም ከጤና ትምህርት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ትምህርቶችን እንዲማር መወሰኑን የጠቆሙት ዶክተር አንዷለም በህክምና ፋርማሲ፣ በህክምና ላብራቶሪ ሳይንስ እንዲሁም በህክምና ላቦራቶሪ በመረጠው ዘርፍ እንዲማርና ባችለር ኦፍ ባዮሜዲካል ሳይንስ እንዲሰጠው መወሰኑን ገልጸዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል፡፡

ዶክተር አንዷለም ተማሪው የአካል ጉዳት እያለበት ለህክምና ትምህርት ዘርፍ መመደቡና ለደረሰው ችግር ዋንኛ ምክንያት የህክምና ኮሌጁ ተማሪዎችን ራሱ መመልመል ያለመቻሉ መሆኑን አብራርተዋል።

የህክምና ኮሌጁ እና የትምህርት ክፍሉ አስቀድሞ ማድረግ የሚገባውን ነገር ማድረግ ባለመቻሉ በተማሪ ቢንያም ላይ ለተከሰተው ችግር ኃላፊነት እንወስዳለን ብለዋል፡፡