“ፍቅርን እንትከል ጥላቻን እንንቀል” በሚል መሪ ቃል የአርንጓዴ አሻራ መርኃ ግብረ ተካሄደ

ሐምሌ 5/2014 (ዋልታ) “ፍቅርን እንትከል ጥላቻን እንንቀል” በሚል መሪ ቃል 4ኛውን ከተማ አቀፍ የአርንጓዴ አሻራ መርኃ ግብረ ተካሄደ፡፡

የአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ 4ኛውን ዙር የአርንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርኃ ግብር በዛሬው ዕለት በእንጦጦ ፓርክ በተዘጋጀው ቦታ ችግኝ ተከላ አከናውኗል፡፡

የቢሮው ኃላፊዋ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) ሁሉም አካል ችግኝ በሚተክልበት ወቅት ስለ ሀገር ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነትን እና መተባበር በማሠብና በመተግበር መልካም የሆኑ እሴቶችን በመዝራትና በትውልዱ በማስረፅ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በመርኃ ግብሩ ላይ የቢሮው አመራሮችና ሠራተኞች፣ ከቲያትር ቤቶች የተወጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች፣ የሆቴል ባለንብረቶች ንግድ ዘርፍ ማኅበር አመራሮቸና አባላት፣ የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚዎች ማኅበር አመራሮችና አባላት እና የቱሪስት ታክሲ ማኅበራት አባላት ጥምረት መሳተፋቸውን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡