አሸባሪው ኦነግ ሸኔ በጎረቤት አገራት መደበቁን መንግሥት ገለጸ

ሐምሌ 7/2014 (ዋልታ) የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እየወሰዱ ባለው እርምጃ አሸባሪው ኦነግ ሸኔ ከመዳከም አልፎ ወደ ጎረቤት አገራት በመሸሽ መደበቁን መንግሥት አስታወቀ፡፡

በአሸባሪው ሸኔ ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በተመለከተ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አሸበሪ ቡድኑን ማዳከም መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

ቡድኑ እየተወሰደበት ባለው እርምጃ እየተዳከመ ቢሆንም የውሸት መረጃዎችን በማሰራጨት ለጥፋት ኃይሉ ሽፋን የሚሰጡ ግለሰቦች መኖራቸውን የጠቆሙ ሲሆን ሁኔታው በሕዝብ ዘንድ መጠራጠርን ለመፍጠር ታስቦ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በወለጋ አሸባሪው ቡድን ጥቃት ላደረሰባቸው ዜጎች መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የአሸባሪዎቹ አላማ ከውጭ ባንዳዎች ጋር በመተባበር ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ተስፋ እንዲቆርጥ ማድረግ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጋር በመቆም የህግ ማስከበር ዘመቻውን እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡