በጎንደር፣ በወራቤና በጅንካ ግጭት በፈጠሩ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመሰረተ

ሐምሌ 7/2014 (ዋልታ) ፍትህ ሚኒስቴር እና ፌደራል ፖሊስ በጋራ በመሆን ባደረጉት ምርመራ በጎንደር፣ በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ እና በደቡብ ኦሞ ጅንካ ከተማ ሃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ ግጭት እንዲቀሰቀስ ያደረጉ እና ማንነትን መሰረት ያደረጉ ወንጀሎችን በፈፀሙ ግለሰቦች ላይ ክስ ተመስረተ።

በጎንደር ከተማ ሚያዚያ 18 ቀን በተቀሰቀሰ ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ ግጭት እንዲቀሰቀስ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ 103 ግለሰቦች ተይዘው ክስ እንደተመሰረተባቸው የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በወቅቱ በጎንደር በተቀሰቀሰው ግጭት ሳቢያ ከ20 በላይ የእስልም እና የክርስትና እምነት ተከታዮች ህይወት ማለፉን የተገለጸ ሲሆን ከ100 በላይ ሰዎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡ ከ60 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የንብረት ውድመት መድረሱም ተመላክቷል።

የምርመራ ቡድን አባላቱ በጎንደር በጋራ ባደረጉት ምርመራ ከ509 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው መረጃ በተገኘባቸው ላይ ክስ መመስረቱን ፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በጎንደር የተከሰተውን ግጭትን ወደ ስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ ለማስፋፋት በተደረገው ሙከራ የሁለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 79 የሚሆኑ ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት እንደደረሰ ነው በመግለጫው የተጠቆመው። በወቅቱ በስልጤ ዞን 46 ሚሊየን ብር የሚገመት የንብረት ውድመት መከሰቱም ተነግሯል፡፡

በዚህ ግጭት ዙሪያ በተደረገው ምርመራ 97 ተጠርጣሪዎች ተይዘው በአስሩ ላይ ክስ እንደተመሰረተ በመግለጫው ተመላክቷል።

በደቡብ ኦሞ ጅንካና አካባቢው ማንነትን መሰረት ያደረገ ግጭት እንዲቀሰቀስ አድርገዋል ተብለው የተጠረጠሩ ከ500 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑም ተገልጿል።

በዙፋን አምባቸው