የህክምና መሳሪያዎችና መድኃኒቶች አቅርቦት ችግርን ከመሰረቱ ለመቅረፍ አዲስ የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው

ሐምሌ 7/2014 (ዋልታ) የሚስተዋለውን የህክምና መሳሪያዎችና መድኃኒቶች አቅርቦት ችግር ከመሰረቱ ለመቅረፍ አዲስ የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በአዳማ በመካሄድ ላይ በሚገኘው ሀገር አቀፍ የሆስፒታሎች ዓመታዊ የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ላይ ተገኝተው ማጠቃለያ ሰጥተዋል።

በዚሁ ወቅት እንደገለፁት በጤና ተቋማት የሚስተዋለውን የህክምና መሳሪያዎችና መድኃኒት አቅርቦት ችግር ከመሰረቱ ለመቅረፍ አዲስ የህግ ማዕቀፎች እየተዘጋጁ ነው፡፡

የህግ ማዕቀፍ ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልፀው፤ በተለይ በነበሩ የግዥ የህግ ማዕቀፍ ያልተካተቱ ግዥዎችና አሰራሮችን ጭምር በማካተት እየተዘጋጀ መሆኑን አመልክቷል።

የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ፋብሪካዎችን የማምረት አቅም በማሳደግና አዳዲስ አምራቾችን ወደ ሥራ ከማስገባት ባለፈ የውጭ ሀገር ተሞክሮ የታከለበት የጤና ሀብት አሰባሰብና አስተዳደር፣ የሜዲካል አገልግሎት አስተዳደርና አጠቃቀም ላይ ያሉትን ክፍተቶች ለመቅረፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ የጤና ሪፎርም ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በዘርፉ የሚታየውን ኋላቀር አሰራር በዘመናዊ አሰራር ለመተካት ጭምር እንደሆነም ገልጸዋል።

እየተዘጋጀ ያለው የህግ ማዕቀፎች መስከረም ፓርላማው ሥራ ሲጀምር በማፀደቅ በቀጣዩ ዓመት ሥራ ላይ ይውላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የዩኒቨርስቲ ሆስፒታሎችን አቅም ለማሳደግ፣በህክምና ቁሳቁስና በሰው ኃይል በበቂ ሁኔታ ለማደራጀት እየሰራን ነው ያሉት ዶክተር ሊያ በዚህም ግልጽ አሰራርና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችሉ ህጎች፣ደንቦችና አሰራሮች እየተዘጋጁ ናቸው ብለዋል።