በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዓለም ዐቀፍ አጋሮች ቁልፍ ሚና መወጣት እንዳለባቸው ተገለጸ

ሐምሌ 7/2014 (ዋልታ) በአፍሪካ ድህነትን ለማስወገድ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዓለም ዐቀፍ አጋሮች እና የግሉ ዘርፍ ቁልፍ ሚና በሚገባ መወጣት እንዳለባቸው የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሐመት አሳሳቡ።

የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሚሳተፉበት 41ኛው የአፍሪካ ኅብረት ሥራ አስፈፃሚ መደበኛ ስብሰባ እየተካሄደ ነው፡፡

በዛምቢያ ዋና ከተማ ሉሳካ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው ስብሰባ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ ልዑክ እየተሳተፈ ይገኛል።

መደበኛ ስብሰባው ሲጀመር የኅብረቱ ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሐመት ባደረጉት ንግግር በአፍሪካ ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር በማምጣቱ ረገድ ተጨባጭ ውጤቶች እየታዩ መሆኑን ገልጸዋል።

ሊቀ መንበሩ በአህጉሪቱ ድህነትን ለማስወገድ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ ለሚሠሩ ሥራዎች ዓለም ዐቀፍ አጋሮች እና የግሉ ዘርፍ ቁልፍ ሚና ይበልጥ መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።

አፍሪካ ኅብረት ተቋማዊ ማሻሻያዎችን በመተግበር ላይ እንደሆነ በንግግራቸው ያስታወሱቱ ሙሳ ፋኪ መሐመት፣ ማሻሻያዎቹ ኮሚሽኑን ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርጉት ናቸው ብለዋል።

የስብሰባ አዘጋጅ ዛምቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስታንሌ ካኩቦ አፍሪካ ኅብረት በዚህ ዓመት በአጀንዳነት የያዘውን የምግብ ዋስትና እና የተመጣጠነ ምግብን በአህጉሪቱ ለማረጋገጥ ግብርናን በማዘመኑ ላይ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በኢንቨስትመንት እና ንግድ ዘላቂ ዕድገትን ለማምጣት የአፍሪካ ሰላም ግምባታ ላይ መዕዋለ ንዋይዋን ማዋል አለባትም ብለዋል።

ስብሰባው የአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል ራሱን ችሎ በሚሠራበት ሁኔታ ላይ ተጨማሪ ሥልጣን ስለመስጠት ይመክራል።

በመደበኛ ስብሰባው የቀጣዩ ዓመት የኅብረቱ በጀት የሚፀድቅ ሲሆን በቅርቡ ለተመሠረተው የአፍሪካ መድኃኒት ኤጀንሲ ዋና መቀመጫ አስተናጋጅ ሀገር የሚመረጥም ይሆናል።

በተጨማሪም የኅብረቱ ተቋማዊ የማሻሻያ ሥራዎች የደረሱበት ደረጃ በመገምገም አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከ41ኛው የአስፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ በተጨማሪ በሉሳካ የኅብረቱ ቢሮ አባላት እና የክፍለ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቦች ሊቃነ-መናብርት የሚሳተፉበት ቅንጅታዊ ጉባኤም ይካሄዳል።