ህግ ተላልፈው የተገኙ ከ367 ሺሕ በላይ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

ሐምሌ 8/2014 (ዋልታ) በ2014 በጀት ዓመት በተደረገ የዋጋ ማረጋጋትና ህገ-ወጥነት ቁጥጥር ህግ ተላልፈው በተገኙ 367 ሺሕ 880 ነጋዴዎችና የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

በበጀት ዓመቱ ከፌዴራል አስከ ወረዳ ባለው የሚኒስቴሩ መዋቅር ዋጋ የማረጋጋት፣ ህገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ቁጥጥር ግብረ ኃይል በተሰሩ ሥራዎች ህግ ተላልፈው በተገኙ 192 ሺሕ 850 ነጋዴዎች ላይ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ 167 ሺሕ 592 የንግድ ተቋማትን የማሸግ፣ 3 ሺሕ 741 ነጋዴዎችን ከንግድ ሥራ የማገድ እርምጃዎች የተወሰዱ ሲሆን 1 ሺሕ 723 ነጋዴዎች ደግሞ ክስ ተመስርቶባቸዋል ነው የተባለው፡፡

እርምጃ የተወሰደባቸው ያለንግድ ፈቃድ ሲነግዱ የተገኙ፣ ያለደረሰኝ የተገበያዩ፣ በምርቶች ላይ ባዕድ ነገር ቀላቅለው ለገበያ ያቀረቡ፣ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ምርቶች ለገበያ ያቀረቡ እንዲሁም ያለአግባብ ዋጋ የጨመሩ መሆናቸው ተገልጿል።

እርምጃው የመሸጫ ዋጋ ዝርዝር ያልለጠፉ እና ምርትን ያለአግባብ በክምችት የያዙ ነጋዴዎችንም እንደሚያካትት የንግድ ሥርዓትና ላይሰንሲንግ ዘርፍ አማካሪ ግዛው ተክሌ የዘርፉን የ2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ለሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች ባቀረቡበት ወቅት አብራርተዋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት አመራሮች በተቋማቱ የ2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀምና የ2015 በጀት ዓመት እቅድ ላይ በአዳማ ከተማ እየተወያዩ እንደሚገኙ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW