በመጪው የትምህርት ዘመን ከመመሪያው ውጭ ወርሃዊ የክፍያ ጭማሪ ማድረግ በሕግ ያስጠይቃል

 

ሐምሌ 8/2014 (ዋልታ) ትምህርት ቤቶች በ2015 የትምህርት ዘመን ከመመሪያው ውጭ ወርሃዊ የክፍያ ጭማሪ ማድረግና ሌሎች የአገልግሎት ክፍያ እንዳይጠይቁ የአዲስ አበባ የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን አሳሰበ።

የባለሥልጣኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ፍቅርተ አበራ እንደገለጹት ከመመሪያው ውጭ የክፍያ ጭማሪ በሚያደርጉ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ እርምጃ ይወሰዳል።

መመሪያው በ2014 ዓ.ም ጭማሪ ያደረጉ የግል ትምህርት ቤቶች በ2015 የትምህርት ዘመን ምንም አይነት ጭማሪ እዳያደርጉ ያዛል።

ነገር ግን መመሪያውን በመጣስ አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች አስቀድመው በደብዳቤና በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ጭማሪ እንደሚያደርጉ ለወላጆች መልዕክት እያስተላለፉ መሆኑ ተደርሶበታል ብለዋል።

መመሪያውን በሚጥሱ ትምህርት ቤቶች ላይ ፈቃድ የመሰረዝና በሕግ የማስጠየቅ እርምጃዎች እንደሚወስድ ከወዲሁ አሳስበዋል።

በከተማው 1ሺሕ 590 የግል ትምህርት ቤቶች ያሉ ሲሆን በ2014 የትምህርት ዘመን 1ሺሕ 77 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ወርሃዊ የክፍያ ጭማሪ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

ቀሪዎቹ ትምህርት ቤቶች በሚያቀርቡት ፕሮፖዛል እና ከወላጅ ጋር በሚያደርጉት መግባባት ጭማሪ ማድረግ እንደሚችሉም መመሪያው ያዛል።

ነገር ግን መመሪያው ጭማሪ ማድረግ በማይፈቅድላቸው ትምህርት ቤቶች ጭማሪ በመጠየቅና ሌሎቹ ደግሞ የተጋነነ ክፍያ አስቀድመው ለወላጆች በማሳወቅ ላይ መሆኑ ተደርሶበታል ብለዋል።

ማንኛውም ትምህርት ቤት ከመደበኛ የአገልግሎት ክፍያ ውጭ በአይነትም ሆነ በገንዘብ ክፍያ መጠየቅ እንደማይችሉ ምክትል ሥራ አስኪያጇ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ ዓለም ዐቀፍ ትምህርት ቤቶችን ሳይጨምር በወር እስከ 15 ሺሕ ብር ክፍያ የሚጠይቁ ትምህርት ቤቶች እንዳሉም ጠቁመዋል።

ይህ የተጋነነ የትምህርት ቤት ክፍያ የኅብረተሰቡን የመክፈል አቅም እየተፈታተነ በመሆኑ መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ወላጆች ባልተስማሙበትና ከባለሥልጣኑ እውቅና ውጭ የተጋነነ ጭማሪ ያደረጉ ትምህርት ቤቶች ላይ ጭማሪውን ለወላጆች ከመመለስ ባሻገር እርምጃ የተወሰደባቸውም እንዳሉ አብራርተዋል።

ወላጆች እነዚህን ትምህርት ቤቶች በማጋለጥና የመማር ማስተማር ሥርዓቱ በአግባቡ እንዲመራ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሕብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ጫና ከግምት ውስጥ በማስገባት አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ላለፉት ሦስት አራት ዓመታት ምንም ዓይነት ጭማሪ ባለማድረጋቸው ምክትል ሥራ አስኪያጇ ምስጋና አቅርበዋል።