የ70 ዓመቱ አዛውንት ከቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ ተመረቁ

ሐምሌ9/2014(ዋልታ) የ70 ዓመቱ አዛውንት ዓሊ ሳፋ ከቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት በሁለተኛ ዲግሪ ተመረቁ።
አሊ ሳፋ የዩኒቨርሲቲው የ9ኛ ዙር ተመራቂዎች ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል።
“የእድሜዬ መግፋት ከትምህርት ፍላጎቴ አላስቀረኝም” ያሉት ዓሊ ስምንት ልጆችና አራት የልጅ ልጆች አያት መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከ35 አመት በፊት እንዳገኙ ያስታወሱት አዛውንቱ ፤ ለትምህርት ባላቸው ፍቅር የተነሳ የዕድሜያቸው መግፋት ሳይገድባቸው በ70 ዓመታቸው ዛሬ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለመቀበል መብቃታቸውን ገልጸዋል።
ልጆችን በማሳደግና በማስተማር ኃላፊነት የተነሳ ከሚወዱት ትምህርት ለዓመታት ርቀው ቢቆዩም ትምህርት ዕድሜ አይገድበውም እንዲሉ ሁኔታዎች በተመቻቹላቸው ጊዜ ለመማር ሳይሰንፉ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከተቀበሉ ከ35 ዓመታት
በኋላ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለመያዝ በቅተዋል።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ በሙያቸው አገራቸውን ያገለገሉት አዛውንቱ አሊ በጡረታ ላይ ቢሆኑም ትምህርት ቤት ለመሄድ ያገዳቸው ነገር የለም።
በመሆኑም ቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ በመግባት ዕውቀት ገብይተው በማርኬቲንግ ማኔጅመት በሁለተኛ ዲግሪ መመረቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
“ትምህርት ለዚህች ዓለም ችግሮች መፍቻ ቁልፍ መሆኑን የሚናገሩት ዓሊ ሳፋ እውቀት እድሜ አይገደበውም” ብለዋል።
በተለይ ልጆች እንዲማሩ ከመገፋፋት ጎን ለጎን ተምሮ አረአያ መሆን ትውልድ ለመቅረጽ ወሳኝ እንደሆነ በመግለጽ ምክራቸውን ለግሰዋል።