አሃዱ ባንክ በይፋ ሥራ ጀመረ

ሐምሌ 9/2014 (ዋልታ) በ17 አደራጅ ኮሚቴ አባላት የተጠነሰሰውና አስር ሺሕ ያህል ባለአክሲዮኖች ያሉት አሃዱ ባንክ በዛሬው ዕለት በይፋ ሥራውን ጀምሯል።

ባንኩን በይፋ ሥራ ያስጀመሩት የብሄራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የባንኮች አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አሳስበዋል።

አሃዱ ባንክም የተጠቀማቸውን ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አገልግሎቶች በመክፈቻው ቀን በመተግበሩ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ከፋይናንስ ተቋማት የብድር ተጠቃሚ ዜጎች ከ6 ሚሊየን አይበልጡም ያሉት የብሄራዊ ባንኩ ገዥ ባንኮች እና የቁጠባ ተቋማት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ለሚኖረው ማኅበረሰብ የብድር አገልግሎት በማቅረብ ልማቱን መደገፍ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ባንኩ በ564 ሚሊየን ብር የተከፈለ እና በ702 ሚሊየን ብር የተፈረመ ካፒታል ሥራውን እንደጀመረ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አንተነህ ሰብስቤ ተናግረዋል።

አሃዱ ባንክ በዓመቱ ከሚያቀርበው ብድር 15 ከመቶ ያህሉን ለሥራ ፈጣሪዎች እና አንስተኛ ኢንተርፕራይዞች እንደሚያመቻች ሊቀመንበሩ ተናግረዋል።

በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ በሚገኘው የባንኩ ዋና መስሪያ ቤት ሥራውን የጀመረው አሃዱ ባንክ እስከ መስከረም ሰላሳ ድረስ የቅርንጫፎቹ ብዛት 50 ይደርሳል ተብሏል።

ብሄራዊ ባንክ በቅርቡ ባወጣው የባንኮች ምስረታ አዋጅ መሰረት ዝቅተኛ የመነሻ ካፒታል መጠን 5 ቢሊዮን ብር እንዲሆን ያዛል። በመሆኑም አሃዱ ባንክ በመጭዎቹ 3 ዓመታት ይህን ግብ ለማሳካት እንደሚሰራ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አንተነህ ሰብስቤ ተናግረዋል።

ባንኩ በ 2025 ዓ.ም በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ መሪ ለመሆን ይሰራል የተባለ ሲሆን ለዚህም በቴክኖሎጂ እና በአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ የተሻለ ሆኖ ቀርቧል ተብሏል።

በእንየው ቢሆነኝ