የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አመራሮችና ሰራተኞች በሀዲያ ዞን ሾኔ ወረዳ ችግኝ ተከሉ

ሐምሌ 9/2014 (ዋልታ) በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተለያዩ ዘርፎች የሚሰሩ አመራሮችና ሰራተኞች በአራተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መረኃ ግብር ሀገር በቀል ችግኞችን በሀዲያ ዞን ሾኔ ወረዳ በመትከል የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡

በመርኃ ግብሩ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያዊያን የዛፎችን ጥቅም ተረድተው መትከል ከጀመሩ ከአንድ ሺህ ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ ታሪክ ቢያወሳም፤ በድርቅ፣ በልቅ ግጦሽና በደን ምንጣሮ ምክንያት የደን ሽፋናችን በእጅጉ ተመናምኖ ይገኛል ብለዋል።

ባለፍት ሶስት ዓመታት የደን ሽፋናችንን ለማሳደግ በተደረገው ከፍተኛ ጥረት 18 ቢሊየን ችግኝ በመተከሉ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር ዘርፈ ብዙ ውጤቶች ተገኝተዋል ብለዋል ሚኒስትሩ።

የሚኒስቴሩ ሰራተኞችና አመራሮች ከአዲስ አበባ በሀዲያ ዞን ሾኔ ወረዳ ድረስ በመሄድ ችግኝ መትከላችን፤ የአረንጓዴ ልማት ስራችን አርዓያ ለመሆንና የሾኔ ከተማ ነዋሪ አሻራችንን ተንከባክቦ ለውጤት እንደሚያበቃ በማመን ነው ሲሉም አክለዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሰራተኞች በ4ተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መረኃ ግብር የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ ሲሆን ኢትዮጵያም 6 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል የያዘችውን ውጥን ለማሳካት የራሱን ሚና እንዳለው ተነግሯል፡፡

ደረሰ አማረ (ከሾኔ)