ተዘርቶ የነበረው የመለያየት አስተሳሰብ እየጠፋ የወንድማማችነት አስተሳሰብ እንዲተካ እየተሠራ ነው – ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)

ሐምሌ 10/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ ከ30 ዓመታት በፊት ተዘርቶ የነበረው የመለያየት አስተሳሰብ እየጠፋ የወንድማማችነት አስተሳሰብ እንዲተካ እየተሠራ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ  የሕዝብና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት በ2014 በጀት ዓመት ያከናወናቸውን ተግባራት በባሕርዳር እየገመገመ ነው።

ከግምገማው ባሻገር የፓርቲው የ2015 የዕቅድ ኦሮንቴሽንም እንደሚያደርግና ለተሳታፊዎቹ ስልጠና እንደሚሰጥ  ተመላክቷል።

የፓርቲው የሕዝብና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት ዘርፍ  ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) የመጠራጠር ትርክት ሳይሆን አንድነት እንዲጠናከርና ወንድማማችነት እንዲጎለብት እየተሠራ  መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የብልጽግና እሳቤዎችን በማስረፅ እና ኢትዮጵያዊያንን በብሔራዊ አንድነት የማስተሳሰር ሥራ መሠራቱንም  ነው የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያ በኅልውና አደጋ ውስጥ በነበረችበት ጊዜ የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና የዓለም ዐቀፍ ግንኙነት ዘርፍ በብቃት መሥራቱንም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ በጠላቶች እንደማትፈርስና ጠላቶቿን እያፈረሰች እንደምትቀጥል ያረጋገጥንበት ወቅት ነው ያሉት ኃላፊው ያለፈው ዓመት በሰላማዊ መንገድ የመንግሥት ምሥረታ የተደረገ መሆኑንም አስታውሰዋል።

በየአካባቢው ያሉ የፅንፈኝነት እንቅስቃሴዎች ከሕዝብ ተነጥለው እንዲመቱና የሕዝብ አንድነት እንዲጠበቅ የተሠራው የሕዝብ ግንኙነት ሥራ መልካም የሚባል እንደሆነም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን የብሔር እና የዘር ፓርቲያቸውን አፍርሰው ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ያለበት ፓርቲ መመስረታቸውና የጋራ ጉባኤ ማካሄዳቸውንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያውያን ላይ እየተካሄደ ያለውን የሀሰተኛ የሚዲያ ዘመቻን በመመከትና የኢትዮጵያውያን አንድነት እንዲፀና የተሠሩ መልካም ሥራዎች መኖራቸውንም አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያውያን በሀሰተኛ የሚዲያ ዘመቻ እንደማይለያዩ የታየበት መሆኑን ጠቁመው  የኢትዮጵያዊያንን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ለመጠበቅ የሚያስችል የሕዝብ ግንኙነት ሥራ እንደሚጠበቅ ማስገንዘባቸውን አሚኮ ዘግቧል።