ድሬዳዋን ፈጣን ወደሆነ የልማት እንቅስቃሴ ለማስገባት አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን – የከተማዋ ተወላጅ ዲያስፖራዎች

ሐምሌ 11/2014 (ዋልታ) ድሬዳዋን ፈጣን ወደሆነ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ለማስገባት አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ የከተማዋ ተወላጅ ዲያስፖራዎች ተናገሩ።

ወደ ከተማችን መጥተን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መመልከታችን በከተማችን ላይ ኢንቨስት እንድናደርግ ያግዘናል ሲሉም ነው የገለፁት።

ወደ ድሬዳዋ የሚመጣው ዲያስፖራ ድሬዳዋን መደገፍና ቱሪዝሙን ከፍ ማድረግ ይችላል ያሉት የዲያስፖራ አባላቱ እንደከተማው ተወላጅነታችን ለከተማችን አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ሲሉ ለዋልታ ተናግረዋል።

ድሬዳዋ በአሁኑ ወቅት አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባት ከተማ እንደሆነች የገለፁት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር በተለያዩ ዓለም አገራት የምትኖሩ የከተማዋ ተወላጅ ዲያስፓራዎች ባላቹ እውቀትና ሀብት ወደ ከተማዋ በመምጣት ኢንቨስት ልታደርጉ ይገባል ብለዋል።

ወደ ከተማዋ በመምጣት ኢንቨስት ለሚያደርጉ የከተማ ተወላጅ ዲያስፖራዎች ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ከንቲባው ተናግረዋል።

የናፍቆት ድሬዳዋ ሳምንት ከሐምሌ 11 ጀምሮ ለተከታታይ አንድ ሳምንት በተለያዩ መርኃ ግብሮች በድሬዳዋ ከተማ ይካሄዳል።

ሱራፌል መንግስቴ (ከድሬዳዋ)