በአሸባሪው ሸኔ ላይ በተወሰደ እርምጃ እንቅስቃሴውን መግታት መቻሉ ተነገረ

ሐምሌ 20/2014 (ዋልታ) የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ሀይሉ አዱኛ በ2014 በጀት አመት የተያዙ እቅድ አፈፃፀምና በ2015 በጀት የተያዙ የልማት እቅዶችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

ኃላፊው መግለጫው እንደገለፁት አሸባሪው ሸኔ በክልሉ መጠነ ሰፊ ጥፋቶችን መፈፀሙንና የፀጥታ ችግሮችን ለመቅረፍ በጠላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል።

በዚህም በአሸባሪው ሸኔ ላይ በተወሰደ እርምጃ እንቅስቃሴውን መግታት መቻሉን የገለፁ ሲሆን ብዙ ጠላት ተደምስሷል፣ ተማርኳል፣ በርካታ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር ውሏል ብለዋል።

በአሸባሪው ሸኔ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጨባጭ ውጤቶችን እያስገኘ ቢሆንም አሁንም ሕዝባችን ከፀጥታ ስጋት አልተላቀቀም ያሉ ሲሆን ይህንን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር በትኩረት ይሰራል በማለት ገልፀዋል።

ኃይሉ አዱኛ አክለው ሕዝብ ተደራጅቶና ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት የአካባቢውን ሰላም እንዲጠብቅ አስቻይ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

የሕዝብና የመንግሥት የፀጥታ አካላትን ትስስር በማጠናከር ሁለንተናዊ ሰላም ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል ያሉት ኃላፊው ሕዝባችንን ከፀጥታ ስጋት ለማላቀቅ በጠላት ላይ እየተወሰደ ያለውን የተቀናጀ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

በደረሰ አማረ