የዓለም የምግብ ድርጅት በዋግ ኽምራ ዞን የመጀመሪያ ዙር የምግብ ስርጭት እያጓጓዘ ነው

ሐምሌ 20/2014 (ዋልታ) የዓለም የምግብ ድርጅት በዋግ ኽምራ ዞን ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የመጀመሪያ ዙር የምግብ ስርጭት እያጓጓዘ መሆኑን አስታወቀ።

ደራሽ ምግብ የያዙ የጭነት መኪናዎች ለዋግ ኽምራ ዞን አበርገሌ፣ ፅግብጂ እና ዝቋላ ወረዳዎች በዓመት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ደራሽ ምግብ እያጓጓዙ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ይሁን እንጂ እየተጓጓዘ ያለው የምግብ ዓይነት እና መጠን ዙሪያ የተገለጸ ነገር የለም፡፡

የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እጅግ አስከፊ አደጋ የሚያስከትል በመሆኑ እነዚህ ህይወት አድን የምግብ አቅርቦቶች መቀጠል እንዳለባቸው የዓለም የምግብ ድርጅት መረጃ አመላክቷል፡፡

የዋግ ኽምራ ዞን በሰሜኑ ጦርነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ በተሰየመው ሕወሓት በወረራ ተይዘው ከነበሩ የአማራ ክልል ዞኖች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወሳል፡፡