የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 27 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ማትረፉን አስታወቀ

ሐምሌ 21/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2014 በጀት ዓመት 27 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ከታክስ በፊት ማትረፉን አስታውቋል፡፡
ባንኩ የ2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ላይ ግምገማ እያካሄደ ነው።
የእቅድ ክንውን ሪፖርት ያቀረቡት የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቤ ሳኖ በበጀት ዓመቱ ባንኩ ከታክስ በፊት 27 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ትርፍ ማግኘቱን ገልጸው ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ49 ነጥብ 3 በመቶ ብልጫ አሳይቷል ብለዋል።
አጠቃላይ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ወደ 890 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ማሳደግ የተቻለ ሲሆን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ11 በመቶ እድገት አሳይቷል።
5 ነጥብ 4 ሚሊየን የሲቢኢ ብር፣ 5 ነጥብ 9 ሚሊየን የሞባይል ባንኪንግ እንዲሁም 39 ሺሕ 22 የኢንተርኔት ባንኪንግ ተጠቃሚዎች አፍርቻለሁም ብሏል ባንኩ።
በመላ ሀገሪቱ ያለ የቅርንጫፍ ቁጥርም 1 ሺሕ 824 ደርሷል ነው የተባለው።
በቀጣይም የአገልግሎት መስጫ ቦታ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ፣ የሀብት ማሰባሰብ ሥራን ማጠናከር እና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሻሻል ላይ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።
የባንኩ ቦርድ ሰብሳቢ ተክለወልድ አጥናፉ የተመዘገቡ ውጤቶች ባንኩን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
ስኬቶችን በ2015 የበጀት ዓመት አጠናክሮ የማስቀጠል እንዲሁም ድክመቶችን የማረምና ማሻሻል ሥራ ይሰራል ብለዋል።
የባንኩ ሀብት 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር መድረሱም ታውቋል።
በትዕግስት ዘላለም