በደቡብ ክልል በአንድ ጀምበር 100 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርኃ ግብር እየተካሄደ ነው

ሐምሌ 21/2014 (ዋልታ) በደቡብ ክልል በአንድ ጀምበር 100 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል መርኃ ግብር ዛሬ በስልጤ ዞን ተጀምሯል።

የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርኃ ግብሩን በስልጤ ዞን ስልጢ ወረዳ በመገኘት በይፋ ያስጀመሩት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው እና የግብርና ሚኒስትር ኡመር ሁሴን ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በወረዳው ገርቢበር ከተማ ዙሪያ በሚገኘዉ አባያ ሀይቅ ዳርቻ በተከለለ 20 ሄክታር መሬት ላይ የሙዝ ችግኝ ተከላ እየተካሄደ ይገኛል።

ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘዉ መረጃ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባለፉት ሶስት ዓመታት 3 ነጥብ 6 ቢሊየን ችግኞችን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች መትከል ተችሏል።

ከተተከሉት ችግኞች ውስጥ 86 በመቶ የፀደቁ ሲሆን በዘንድሮ 4ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ተገብቷል።

በአረንጓዴ አሻራው የደን፣ የፍራፍሬ፣ የእንስሳት መኖና ለከተሞች ውበት ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ትኩረት መሰጠቱ ተጠቁሟል።

ዛሬ በሚካሄደዉ በአንድ ጀምበር 100 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ በየደረጃዉ እየተሳተፈ ይገኛል።

በደቡብ ክልል በዚህ አመት በጥናት በተለየ 441 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የችግኝ ተከላው እየተካሄደ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

እንደኢዜአ ዘገባ በአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ የሀይማኖት መሪዎችና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW