የአማራ ክልል የ2015 ዓ.ም ጠቅላላ በጀት ከ95 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኖ ጸደቀ

ሐምሌ 21/2014 (ዋልታ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባዔ የክልሉን የ2015 ዓ.ም ጠቅላላ በጀት 95 ቢሊዮን 320 ሚሊየን 119 ሺሕ 600 ብር አጽድቋል፡፡

የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን መሃሪ (ፒኤችዲ) ለምክር ቤቱ የክልሉ የ2015 ዓ.ም ጠቅላላ በጀት 95 ቢሊዮን 320 ሚሊየን 119 ሺሕ 600 ብር ሆኖ እንዲጸድቅ ባቀረቡት መሰረት ነው ምክር ቤቱ በጀቱን ያጸደቀው።

የበጀቱ 50 ነጥብ 1 በመቶ ወይም 47 ቢሊየን 778 ሚሊየን 282 ሺሕ ብር በክልሉ የሚሰበሰብ ገቢ ነው ተብሏል ።

የበጀቱ 46 ነጥብ 6 በመቶው ደግሞ የፌዴራል መንግሥት ጥቅል የቀመር መደበኛ ድጋፍ ድርሻ ሲሆን ይህም 44 ቢሊዮን 379 ሚሊየን 767 ሺሕ 935 ብር ሆኗል ።

ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈፀሚያ የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ 3 ቢሊዮን 24 ሚሊዮን (3 ነጥብ 2 በመቶ) እና ከውጭ ሀገር ዕርዳታ 138 ሚሊየን 69 ሺሕ 665 ብር (0 ነጥብ 1 በመቶ) ነው።

የ2015 በጀት ዓመት የክልሉ አጠቃላይ በጀት ጣራ በ2014 ከተመደበው አንፃር የ15 ቢሊዮን 215 ሚሊየን 450 ሺሕ 203 ጭማሪ ያለው ሲሆን ይህም የ19 በመቶ ዕድገት አለው ነው የተባለው።

ከመንግሥት ግምጃ ቤት ከተመደበው በጀት 85 ቢሊዮን 783 ሚሊየን 387 ሺሕ 935 ብር ውስጥ ለታችኛው የአስተዳደር እርከን 61 ቢሊየን 878 ሚሊየን 294 ሺሕ 500 ብር ሆኖ ተመድቧል ። ይህም 72 ነጥብ 1 በመቶ መኾኑ ነው የተገለጸው።

ለድንገተኛ አደጋዎች እና ክስተቶች የበጀት ፍላጎት በተወሰነ ደረጃ ለመሸፈን የመጠባበቂያ በጀት 3 ቢሊየን 499 ሚሊየን 993 ሺሕ 435 ብር ሲሆን 4 ነጥብ 1 በመቶ ድርሻ እንዲኖረው መመደቡን የአሚኮ ዘገባ አመላክቷል፡፡

ለምክር ቤቱ የቀረበው የ2015 ዓ.ም በጀት አመት ጠቅላላ በጀት በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።