የኅልውና አደጋውን ለመቀልበስ ባለፈው በጀት ዓመት የተሰራው ስራ ውጤታማ እንደነበር የመከላከያ ሚኒስትሩ ተናገሩ

ሐምሌ 22/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ የገጠማትን የኅልውና አደጋ ለመቀልበስ በባለፈው በጀት ዓመት የተሰራው ስራ ውጤታማ እንደነበር የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የበጀት ዓመቱን የስራ ሂደት ግምገማ በማጠናቀቅ የ2015 በጀት ዓመት የስራ እቅድ ላይ ውይይት አድርጓል።

በጦር ኃይሎች ጠቅላይ መምሪያ ለሁለት ቀን የተካሄደውን ዓመታዊ የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ የመሩት ሚኒስትሩ የ2014 ዓ.ም የስራ ሪፖርት ካደመጡ በኃላ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የገጠማትን የኅልውና አደጋ ለመቀልበስ ባለፈው በጀት ዓመት የተሰራው ስራ ውጤታማ ነበር።

እንደ ተቋም ከፍተኛ የሀገር ሃብትን የሚያስወጡ የምርት ግብዓቶችን ከመግዛት ይልቅ አምራች ስራ ላይ በመሳተፍ ወጪን የመቀነስ ስራ መስራት ለበለጠ ግዳጅ ብቁ እንደሚያደርግ አንስተዋል።

የ2015 በጀት ዓመት እቅድ በ2014 በጀት ዓመት የነበሩ እጥረቶችን የሚሞላ ስራ መስራት ይገባልም ብለዋል፡፡

በአዲሱ በጀት ዓመት ቀዳሚ የሆነውን የዝግጁነት ስራ ከመስራት ጎን ለጎንም ተቋማዊ ኢንዱስትሪዎችን የማጠናከር፣ በራስ አቅም ማምረት እና የሠራዊቱን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ተጨማሪ አማራጮችን በመውሰድ ግንባታዎችን ማከናወን እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

የኢንዱስትሪ ተቋማት ትርፋማነታቸውን የሚያሰፉ ስራዎችን አጠናክሮ በመስራት የሰራዊቱንና የቤተሰቡን ኑሮ የሚያቀሉ፣ መከላከያ ፋውንዴሽን የጀመራቸው በሁርሶ እና በብላቴ ማሠልጠኛ ማዕከል የሚሰሩ የግብርና ስራዎችን በሌሎችም በማስፋት በምግብ ምርቶች እራስን የመቻል ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ መመሪያ መስጠታቸውን ከመከላያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።