የሥነ-ምግባር ጥሰት በፈፀሙ 120 አመራርና ሠራተኞች ላይ እርምጃ መውሰዱን አገልግሎቱ ገለፀ

ሐምሌ 22/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተገናኘ ብልሹ አሰራር ሲከተሉና የሥነ-ምግባር ጥሰት ሲፈፅሙ በተገኙ 120 አመራርና ሠራተኞች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱን ገለፀ።

በተቋሙ የፀረ ሙስናና ስነ ምግባር ዳይሬክተር ህብረወርቅ ይመኑ እርምጃው የተወሰደው በአገልግሎት አሰጣጥ ወቅት ከደንበኞች በቀረበ ቅሬታ መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።

የግልጽነትና ተጠያቂነት ስርዓትን ለማስፈን እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተሩ በ2014 በጀት ዓመት አገልግሎቱ ተገልጋዮች ጥቆማ ማቅረብ የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር 145 ጥቆማዎችን ተቀብሎ የማጣራት ስራ መስራቱን ገልፀዋል።

በዚሁ መሰረት የተቋሙን የሥነ ምግባር ደንቦችና የአሰራር ስርዓቶች የሚጥሱ አመራርና ሠራተኞችን ተጠያቂ በማድረግ ለተፈፀሙ ጥፋቶች ተመጣጣኝና አስተማሪ እርምጃዎች መወሰዳቸውን አስታውቀዋል።

በ221 አመራርና ሠራተኞች ላይ የቀረቡ ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ ማጣራት ተደርጎ በ120ዎቹ ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን የገለፁት ኃላፊው ቀሪዎቹ 101 ጥቆማዎች በተቋሙ የዲሲፕሊን ኮሚቴ በመታየት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ከደንበኞች ከቀረቡ የብልሹ አሰራር መገለጫዎች መካከል በሕገ ወጥ መንገድ ቆጣሪ ማስገባት፣ ጉቦ መጠየቅ፣ ደንበኛን ማጉላላት፣ ያለበቂ ምክንያት ስራን ማዘግየት፣ ለአስቸኳይ ጥገና ስራ ደንበኞች ገንዘብ አዋጥተው እንዲከፍሉ ማስገደድ እና ያለደረሰኝ የቆጣሪ ማስገቢያ ክፍያ መቀበል ይገኙባቸዋል።

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከደንበኞች የመጣውን ጥቆማ ጨምሮ ተቋሙ ያስቀመጠውን የውስጥ አሰራር ስርዓት ባላከበሩ እና የሥነ-ምግባር ጥሰት በፈፀሙ በድምሩ 1 ሺሕ 50 አመራርና ሠራተኞች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም ገልፀዋል።

እነዚህም 27 የቃል ማስጠንቀቂያ፣ 356 የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ 568 የደመወዝ/ገንዘብ ቅጣት፣ 24 ከቦታ የማንሳት እና 75 የስንብት እርምጃዎች
መሆናቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ግልፅነትንና ተጠያቂነትን ማስፈን አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ደንበኞች ብልሹ አሰራሮችን በማጋለጥና መብታቸውን በሕጋዊ መንገድ በማስከበር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲወጡ አገልግሎቱ ጥሪ አቅርቧል።