ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አረንጎዴ አሻራቸውን በድሬዳዋ አኖሩ

ሐምሌ 22/2014 (ዋልታ) በድሬዳዋ አዲሱ ምድር ባቡር ጣቢያ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ አካላት የችግኝ ተከላን ጨምሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስነ-ስርዓት አከናወኑ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) እና በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።

“አሻራችን ለትውልዳችን” በሚል መሪ ሃሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ የሚገኘው የአራተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በዚህ የችግኝ ተከላ ስነ-ስርዓት የአስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም ተሳትፈዋል።

ከችግኝ ተከላ ስነ-ስርዓቱ በመቀጠል ዋልታ፣ ፋና እና ዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ያዘጋጁትን ለአንድ ሺሕ ችግረኛ ተማሪዎች የሚሆን የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ አስረክበዋል።

የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል የሆነው የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ መርኃ ግብር መካሄዱን ኢዜአ ዘግቧል።