ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ከኢትዮ ቴሌኮም ሰራተኞች ጋር ችግኝ ተከሉ

ሐምሌ 23/2014 (ዋልታ) የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ከኢትዮ ቴሌኮም የማዕከላዊ ምስራቅ ሪጅን ሰራተኞች ጋር በጋራ የችግኝ ተከላ አከናውነዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ኮምፒውተሮችንና ፕሪንተር በክልሉ ለሚገኘው ሸኪብ አብዱላሂ ሁለተኛ ደረጃ ትምህረት ቤት ድጋፍ አድርጓል።
በድጋፉ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ድጋፉ ተማሪዎችን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መደገፍ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ይረዳል ብለዋል።
በተጨማሪም የመምህራን እና የተማሪዎችን የመማር ማስተማር ተነሳሽነት ያሳድጋል ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ማዕከላዊ ምስራቅ ሪጅን ሥራ አስኪያጅ መሀመድ ሰዒድ በሀረሪ እና ኦሮሚያ ክልል ባቢሌ ወረዳ ላይ ለሚገኙ ሁለት ትምህርት ቤቶች ባጠቃላይ ከ3 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸውን ኮምፒውተሮች በመለገስ የተደራጀ የዲጂታል ላብራቶሪ ማስረከባቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም 20 ሺሕ ችግኞችን በማዘጋጀት 10 ሺሕ የሚጠጉ ችግኞችን በሐረሪ ክልል ሐማሬሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መትከላቸውን ነው ያስታወቁት።
የሐረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙክታር ሳሊህ በበኩላቸው ድጋፉ በተለይም የትምህርት ጥራትን ለማጎልበት እየተከናወኑ በሚገኙ ተግባራት እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
በእለቱ የተደረገው ድጋፍ ኢትዮ ቴሌኮም እንደ ሀገር 64 ሚሊየን ብር በመመደብ ለ66 ትምህርት ቤቶች የዲጂታል ላብራቶሪ የማደራጀት ሥራው አንዱ አካል መሆኑ ተገልጿል።
በመርኃግብሩ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሚስራ አብደላን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የተለያዩ ተቋማት ሰራተኞች ተገኝተዋል።
ተስፋዬ ኃይሉ (ከረር ቅርንጫፍ)