ሚኒስቴሩ በጎንደር ከተማ የበጎ አድራጎት ተግባራትን አከናወነ

ሐምሌ 23/2014 (ዋልታ) የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በጎንደር ከተማ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራትን አከናወነ፡፡
ሚንስቴሩ በጎንደር ከተማ በሁለት ክፍለ ከተሞች የ10 አቅመ ደካማ ቤቶችን የማደስ፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ለሚማሩ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የማድረግ፣ የማዕድ ማጋራትና ከ20 ሺሕ በላይ ችግኞችን የመትከል ተግባራት አከናውኗል፡፡
በተጨማሪም በከተማዋ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ለሚማሩ ለአቅመ ደካማ ቤተሰብ ተማሪዎች የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡
አጋዥ ለሌላቸው ተማሪዎች 1 ሺሕ 807 የተለያዩ ማጣቀሻ መጻሕፍት፣ 3 ሺሕ 600 ደብተሮች፣ 3 ሺሕ እስክርቢቶና 1 ሺሕ 500 እርሳስ በድጋፍ አበርክቷል።
በፕሮግራሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ፒኤችዲ) ሀገር ተረካቢ የሆኑ ተማሪዎችን ማገዝ በጣም ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ተማሪዎችም ጠንክረው በመማር እና በማንበብ ለስኬት እንዲበቁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
አያይዘውም የመተባበር እና የመደጋገፍ ባህልን በማጎልበት የአብሮነት እሴታችንን አጠናክረን ማሻገር አለብን ብለዋል፡፡
ያለንን የማካፈል እና የመረዳዳት ኢትዮጵያዊ ባህላችንን አጠናክሮ በማስቀጠል አንድነትን ማጠንከር እንደሚገባም ሚኒስትሩ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
አመለወርቅ መኳንንት (ከጎንደር)