በክልሉ በአንድ ጀንበር ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ችግኝ የመትከል መርኃ ግብር እየተካሄደ ነው

ሐምሌ 24/2014 (ዋልታ) በጋምቤላ ክልል 4ኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ በአንድ ጀንበር ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን የመትከል መርኃ ግብር እየተካሄደ ይገኛል።

መርኃ ግብሩ ”አሻራችን ለትውልዳችን” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ሲሆን የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልሉ ምክር ቤት አባላት ተሳትፈዋል፡፡

ርዕሠ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ በክልሉ በተያዘው  ክረምት ከ9 ነጥብ 5 ሚሊዮን  በላይ ችግኞችን ለመትከል የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ሁሉም የኀብረተሰብ ክፍሎች በየአካባቢያቸው ችግኞችን በመትከል እና በመንከባከብ ታሪካዊ አሻራቸውን እንዲያኖሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አጃክ ኡቻላ በበኩላቸው መርኃ ግብሩ በሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች ተለይቶ በተዘጋጀ የተከላ ቦታ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡